የኢዜማ የእስካሁን ጉዞ እና የወደፊት አቅጣጫ || ኢዜማ

የኢዜማ የእስካሁን ጉዞ እና የወደፊት አቅጣጫ || ኢዜማ

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት የምንፈልገውን የሁላችንንም መብት የሚያከብር እና ለሁላችንም እኩል ዕድል የሚሰጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጠንካራ መደላድል ላይ እንዲመሰረት ገንቢ አስተዋፅዖ ማድረግን ግንባር ቀደም ዓላማው አድርጎ የተመሰረተ የፖለቲካ ፓርቲ ነው። ኢዜማ ሀገራችን ያለችበትን አስቸጋሪ እና ውስብስብ ሁኔታ የሚመጥን መዋቅር በመዘርጋት እና የሚጠበቅበትን አመራር በመስጠት አዎንታዊ ሚና መወጣት እንዲችል ስትራቴጂክ ግቦች ነድፎ ለማሳካት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

በየጊዜው በአጠቃላይ ሀገራችን እየሄደችበት ያለው መንገድ እና ያስቀመጥናቸውን ግቦች ብሎም ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት ፓርቲያችን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን ያህል በትክክለኛው መስመር ላይ እንደሆነ ቆም ብሎ መመርመር እና ጉድለቶችን ለይቶ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ ሊለመድ የሚገባው ድርጅታዊ ባህል መሆኑን በማመን የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ አባላት እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት ጥልቅ ውይይት እና ግምገማ አካሂደናል። ይህ በድርጅቱ የአንድ ዓመት ጉዞ ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገው ሰፊ ውይይት እና ግምገማ እንዲደረግ ምክንያት የሆኑት ከሁለት አቅጣጫ በመጡ ግፊቶቸ ነበሩ። የመጀመሪያው የፓርቲውን ሰትራቴጂክ ግብ ለማሳካት እና ሀገራችን ያለችበት ውስብስብ ችግሮች ለመቅረፍ በአመራሩ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አመርቂ ናቸው ወይ? በሚል ከአባላት እና ከአመራሩም መካከል የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው። ሌላኛው ለዚህ ሰፊ ግምገማ መነሻ ምክንያት የሆነው በተለያየ ጊዜ በፓርቲው ደጋፊዎች፣ የማኅበራዊ ሚድያ አንቂዎች፣ ምሁራን አና የፖለቲካ ተንተኞች እንዲሁም በተፎካካሪዎቻችን ጭምር ኢዜማ ሕዝብ በጠበቀው መልኩ አልተገኘም፣ አንድ አንዶች ደግሞ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አንፃር ኢዜማ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ አይደለም፣ ኢዜማ የገዢው ፓርቲ ጋር መስመር ያለፈ ግንኙነት ፈጥሮ የሕዝቡን ጥያቄ ዘንግቶታል የሚሉ የሰላ ትችቶች በመደጋገማቸው እራሳችንን ለመገምገም መነሻ ምክንያት ሆኖናል።

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የተደረገው ውይይት ሦስት ቅርፅ ነበረው። የመጀመሪያው ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተመረጡ ሰዎች ያዘጋጁዋቸው የግምገማ መነሻ ጽሑፎች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ሁለተኛው ከፓርቲው ፍፁም ገለልተኝ የሆኑ እና የሀገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ በመከታተል የሚታወቁ ሶስት የፖለቲካ ተንታኞች ባቀረቡት መነሻ ወረቀቶች የተደረገ ውይይት ነው። በመጨረሻም በአመራሮቹ እና ሦስቱ ገለልተኛ ተንታኞች ያቀረቧቸው ጽሑፎች እና የተደረጉትን ውይይቶች መሰረት በማድረግ ለተጨማሪ ውይይት 5 አጀንዳዎች ተመርጠው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የተዘጋጀው አንደኛው ወረቀት «ያለንበት እና እየሄድንበት ያለው መንገድ ትክክል አና ስትራቴጂክ ግባችንን ለመምታት የሚያስችል ነው።» በሚል ከኢዜማ ስትራቴጂክ ግብ ጋር በማሰናሰል የተሠሩ ሥራዎችን እና የያዝናቸው አቋሞች ያመጡትን ውጤት ያቀረበ ሲሆን፤ ሁለተኛው ወረቀት ደግሞ «እየሄድንበት ያለው መንገድ ድጋፍ እያሳጣን እና ወደ ምንፈልገው መንገድ እየወሰደን አይደለም፤ ስለዚህም የአካሄድ ለውጥ ማድረግ አለብን።» በሚል ለዚህ ማሳያ ይሆናሉ ያሏቸውን ሀሳቦች አና በተለይ ከላይ ለግምገማው እንደ መነሻ ምክንያት የሆነውን ደጋፊዎቻችን እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ኢዜማን አስመልክቶ የሚያነሱትን ቅሬታ በማጣቀስ የተደራጀ ሀሳብ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ቀርቧል።

በፓርቲው አመራሮች የተዘጋጁት ሁለቱ የጥናት ወረቀቶች ከላይ በተገለፀው መልኩ ቀርበው ውይይት ከተካሄደ በኋላ ፓርቲው ራሱን ሲገመግምም የሚጎለውን ገለልተኝነት (biase) ለማጥራት የፓርቲው አባል ያልሆኑ ኢዜማን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ የሚታወቁ ሶስት የፖለቲካ ተንታኝ፣ ምሁር እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ኢዜማን አስመልክቶ ጽሑፍ እንዲያቀርቡ በተጋበዙት መሰረት አቅርበዋል።

እነዚህ ከኢዜማ ገልለተኛ የሆኑ ተጋባዦች አጠቃላይ የሀገራችን የለውጥ ሂደት እና አሁን ያለችበት ሁኔታን እንዲሁም ኢዜማን በተመለከተ ያላቸውን አስተያየት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱ ላይ ከተነሱት ሀሳቦች መካከል፦

1. ኢዜማ የተለያዩ ጠንካራ ድርጅቶች እራሳቸውን አክስመው አንደመሰረቱት ፓርቲ ከምትጠበቁት በተቃራኒ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዩች ላይ ዝምታ ታበዛለችሁ፤ ከሌሎች ፓርቲዎች ልቃችሁ ስትወጡ አትታዩም። የኢዜማ ዝምታ ብቻውን ሀገር ያድን ይመስል ዝምታችሁ የእንቅልፍ ያክል ሆኗል። መዋቅራችሁን ወረዳ ድረስ መዘርጋቱ ተገቢ ቢሆንም ስር የሰደደ ዝምታችሁ የብሔር ድርጅቶች አንድም ቢሮ ሳይኖረቸው ጥቃቅኗን አጀንዳ በማጮህ እና በማጉላት በማኅበረሰቡ ዘንድ ጎልተው እንዲታዩ ሆነዋል።

2. እንደ ፓርቲ ሕዝባዊ መሰረታችሁን መለየት እና ለእነሱ ትኩረት መስጠት አለባችሁ፣ እሱን እያጣችሁ ነው።

3. የሀገራች የሽግግር ሂደት ወዴት እየሄደ እንደሆነ ግልፅ አይደለም፤ ወደ ዴሞክራሲ፣ ወደ የግለሰብ አምባገነንት ወይንም ወደ ዘውጋዊ አምባገነን አገዛዝ ሊያመራ የሚችልበት ዕድል አለ።

4. የገዢውን መንግሥት ክፍተት አሳንሳችሁ በማየት በሚፈጠሩ ክስተቶች ላይ ተከታታይ መግለጫ አታወጡም።

5. ስድተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማራዘም የተሄደበትን መንገድ እና በተራዘመው ጊዜ ገዢው ፓርቲ የሥልጣን ገደብ ሊደረግበት አንደሚገባ አጥብቃችሁ መከራከር ነበረባችሁ።

6. ኢዜማ የተከተለው ወረዳን መሰረት ያደረገ አደረጃጀተን አና የዘረጋውን መዋቅር በጠንካራ ጎን የሚነሳ ነው።

7. ኢዜማ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የተለያዩ ፖሊሲዎች የማዘጋጀት ሥራዎችን መሥራቱ ጥሩ ተግባር እንደሆነ።

8. ትክክለኛ የፌደራል ሥርዓት እንዲተገበር በፕሮግራችሁ ውስጥ ያካተታችሁ እና የምታምኑበት ቢሆንም ፌደራሊዝምን በተመለከተ በብሔር ድርጅቶች በትረክት ተበልጣችኋል።

9. በአመራሮች መካከል እንዲሁም በአባላት እና በአመራር መካከል ያለው የፖለቲካ እይታ እና አረዳድ እንዲሁም ኢዜማን በመግለፅ በኩል ልዩነት አለ።

10. ዜግነትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ከሚለው በዘለለ፣ የመደራጀት መሰረታችሁ የሆነውን እና ዘውግ ዘለል ለሆነ አደረጃጀት የሚጠቅመውን የማኅበራዊ ፍትህ ፍልስፍናን አጉልታችሁ ማቅረብ አልቻላችሁም።

11. ለሚደረግባችሁ የስም ማጥፋት ዘመቻ መልስ ለመስጠት ወደ ኋላ ማለታችሁ ኅብረተሰቡ ውስጥ ላለ ውዥንበር መንስዔ ሆኗል።

12. ለውጥ እንዲመጣ ያደረጋችሁት አስተዋፅዖ ሊሰጣችሁ የሚገባውን የሞራል ልዕልና የኢህአዴግ ካድሬ ለነበሩት በመተው ከእናንተ የተሻለ የሞራል ልዕልና ያላቸው እንዲመስል እያደረጋችሁ ነው፡፡

የሚሉ ሀሳቦች በተጋባዦቹ የተነሱ ሀሳቦች ነበሩ።

በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እና በተጋባዦቹ ከቀረቡት መነሻ ጽሑፎች በኋላ ተጨማሪ ውይይት ሊደረግባቸው እና በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ሊሰጥባቸው ይገባል የተባሉ አምስት አጀንዳዎች ተለይተው ሰፊ ውይይቶች ተደርጎባቸዋል።

አጀንዳ አንድ: የፓርቲው ስትራቴጂክ ግቦች

• ኢዜማ ተልዕኮውን ማስፈፀም የሚችል ዘመን ተሻጋሪ፣ ጠንካራ፣ ተጠያቂነት ያለበት የፖለቲካ ፓርቲ ማድርግ፤

• ኢዜማ ኢትዮጵያን በጠንካራ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ጎዳና መምራት የሚችልና የኅብረተስቡን አመኔታ ያገኘ የመንግሥት ቅርፅ እንዲኖረው ማድረግ፣

• በሀገራችን ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ተቋማዊ ለማድረግ እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር ጉልህ ሚና መጫወት፤ እና

• በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች አብላጫ ወንበር በመያዝ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል መቀመጫዎች ማሸነፍ፤

ሲሆኑ በተደረገው ውይይት ወቅት ፓርቲው በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ተደራሽ የሆነ ጠንካራ የድርጅት መዋቅር በመዘርጋት እና እነዚህ የምርጫ ወረዳ መዋቅሮች በየአካባቢያቸው ያሉ ከኢዜማ ሀሳብ ጋር የሚሄድ አመለካከት ያላቸውን ዜጎች አባል እና ደጋፊ እንዲሆኑ የተሠራው ሥራ ኢዜማ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት ለሚያደርገው ጥረት ጥሩ አስተዋፅዖ እንዳደረገ ተነስቷል። ኢዜማ በኅብረተሰቡ ዘንድ ኃላፊነት የሚሰማው ከሥልጣን በላይ የሕዝብ ደህንነት እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሚያሳስበው ድርጅት ነው የሚል አመለካከት በበቂ ሁኔታ ኅብረተሰቡ ውስጥ እንዳልገባም በውይይቱ ተነስቷል። ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲገነቡ ኢዜማ የተቻለውን ያክል እንቅስቃሴ እንዳደረገ፤ በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች ማንነት ተኮር እና የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግጭቶች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ቢሆንም በየትኛው ቦታ የኢዜማ አባሎች እና ደጋፊዎች ሰላም እና መረጋጋትን ከሚነሳ ጉዳይ ጋር ስማቸው ተነስቶ አያውቅም። ይህም ከግባችን አንፃር እንደስኬት ሊታይ እንደሚገባ በውይይቱ ተነስቷል። የዴሞክራሲ ተቋማትን ከመገንባት አንፃርም አፋኝ የነበሩ ሕጎች በተሻሻሉበት ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ መደረጉም እንደተጨማሪ ጥንካሬ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል። ኢዜማ አባል የሆኑ እና ያልሆኑ በተለያየ መስክ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን እያሳተፈ እያዘጋጃቸው ያሉ የፖሊሲ አማራጮች በምርጫ ውስጥ የምናደርገውን ተሳትፎ ከማገዝ በላይ የሀገራችን ፖለቲካ በሀሳብ እና በምክንያታዊ ውይይት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስተዋፆ ስለሚኖረው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ስምምነት ተደርሷል።

ስትራቴጂክ ግቦቻችን ቅድሚያ የሚሰጡት ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለሰላም እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ነው። በዚህ መሰረት የሀገርን አንድነት እና ደህንነትን፣ የሀገራችን ሰላም እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን አደጋ ውስጥ የሚጥሉ አካሄዶችን ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ድጋፍ ተብሎ የተለየ አቋም መያዝ በፍጹም እንደማይገባ በድጋሚ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የምናወጣቸው መግለጫዎች እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የምንይዘው አቋም ከስትራቴጂክ ግባችን ጋር የማይጋጩ አና ግቦቻችንን ለማሳካት መንገድ መሆን እንደሚገባቸው እና በመንግሥት በኩል ሀገርን እና ሕዝብን የሚጎዱ ድርጊቶች ሲፈፀሙ በግልጽ ድርጊቱን ማውገዝ ተገቢ መሆኑንም ተስማምተናል።

አጀንዳ ሁለት: አሁን ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ እና ለውጡን እንዴት እናየዋለን?

በዚህ አጀንዳ ስር ወሳኝ የሆኑ ነጥቦችን አንስተን የገመገምን ሲሆን የለውጡን ጊዜ ተስፋ ሰጪ የነበሩ ወቅቶች እና አሁን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በዝርዝር አይተናል። ተስፋ ሰጪ እና በጎ ጅምሮች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ወደ ዴሞክራሲ ለሚደረገው ጉዞ እንቅፋት ሆነው የነበሩ አፋኝ ሕጎች ገለልተኛ በሆኑ ባለሙያዎች እንዲረቀቁ እና እንዲፀድቁ መደረጉ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ከፖለቲካ ገለልተኛ በሆኑ ሰዎች እንዲመሩ ጥረት መደረጉ እና ሀገራችንን ወደ እርቅ እና ይቅር መባባል ሊወስዱ የሚችሉ ታዋቂ የሀገራችን ፖለቲከኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን የተካተቱባቸው ብሔረዊ የእርቅ እና ሰላም እንዲሁም የማንነት እና ወሰን ኮሚሽን መቋቋማቸው የለውጡን ጅማሮ ተስፋ ሰጪ ያደረጉት ነበሩ።

የገዢውን ፓርቲ ወደ አንድ ውህድ ፓርቲነት መምጣት እንደ አንድ በጎ አካሄድ የተመለከትነው ቢሆንም እሱን እና የምርጫውን መቃረብ ተከትሎ የገዢው ፓርቲ መዋቅሮች የተለመደ የአፈና ሥራቸው ውስጥ ተዘፍቀው መገኘታቸው በውይይቱ ወስጥ ተነስቷል። በለውጡ ጅማሮ የተበረታታነውን ያህል በለውጡ ወቅት ሀገር እየመራ ያለው ኃይል ላይ ጥያቄ ልናነሳ ይገባል የሚሉ ሀሳቦች በዚህ አጀንዳ ስር ውይይት የተደረገበት ነበር።

በዚህ አጀንዳ ውስጥ በተለያየ ወቅት ኢዜማ ገዢው ፓርቲን ሲገልፅ የታችኛው እና የላይኛው መዋቅር እያለ ለያይቶ መግለፁ ምን ያህል አግባብ ነው በሚል ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በተለይ የታችኛው አመራር ሥልጣኔን እና የተለያየ ጥቅማ ጥቅሜን አጣለሁ ብሎ ስለሚሰጋ አፈናውን የሚያካሂደው ይህ አካል ነው ልንታገለው ይገባል የሚል ሀሳብ እና በፍፁም ብልፅግና ብልፅግና ነው የላይኛው እና የታችኛው አመራር ብለን ለይተን ልናየው አይገባም፣ አንድ ተቋም እሰከሆነ ድረስ የትኛውም አካል ለሚፈፅመው ጥፋት ፓርቲው ኃላፊነት ሊወስድ እና ተጠያቂ ሊሆን ይገባል የሚል ስምምነት ተደርሷል።

ኢትዮጵያ እጅግ የተወሳሰቡና ብልሃት ከጥንቃቄ ጋር የሚሹ ለረጅም ጊዜ የተከማቹ እና ወቅታዊ የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የውጭ አካባቢያዊ ችግሮች ያሉባት ሀገር በመሆንዋ ለእያንዳንዱ ወቅታዊ ሁኔታ የምንሰጠው ምላሽ ይህንን ከግንዛቤ ያስገባ ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን እንደሚገባው አፅንዖት ተሰጥቶበታል።

አጀንዳ ሶስት: ድርጅታዊ ግምገማ፣ የኢዜማ ገጽታ በአባላት በመገናኛ ብዙሃንና በሕዝብ ዘንድ

በዚህ አጀንዳ ስር በፓርቲው ወስጥ ስራን አቅዶ ከመስራት ጀምሮ የተሰሩ ስራዎች እቅድን መሰረት አድርገው መሰራታቸውን የመመርመር (evaluation) ልምድ ሊዳብር እንደሚገባ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የኢዜማን ገፅታ አስመልክቶ በተለይ በማኅበራዊ ሚድያ ፓርቲው ላይ ከፍተኛ የሆነ ስም የማጥፈት ዘመቻ የሚካሄድ መሆኑን ነገር ግን የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ እነዚህን እንደማይመክት፣ በተለያዩ ክስተቶች ላይ ፈጣን መግለጫ አለማውጣት ድጋፍ እንዳሳጣን የተነሱ ሲሆን እነዚህን ሃሰቦች በሚሞግት መልኩ በማኅበራዊ ሚድያ የሚናፈሰውን ተከተትለን አለመሄዳችን ተገቢ መሆኑ፣ በበቂ ደረጃ ባይሆንም በአብዛኛው ሕዝብ ውስጥ ኃላፊነት የሚሰማው እና ትክክለኛ መንገድ ላይ ያለ ፓርቲ እንደሆንን ግንዛቤ አለ የሚሉ መከራከራያዎች ቀርበዋል። እስካሁን ድረስ በመርህ ላይ ተመስርተን በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ አመላካች መግለጫዎችን እየሰጠን የመጣን ቢሆንም በቀጣይ ወቅትን የጠበቀ፣ እውነተኛ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ እና የኢዜማን አቋም ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ደርሰናል።

ከድርጅታዊ ሥራ አፈጻጸም አንጻር የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የእያንዳዱ የሥራ ዘርፍ እንቅስቃሴ በዕቅድ እንዲመራ ማረጋገጥ እና የተሠራውን ሥራ በየጊዜው መገምገም የዓመቱን የሥራ ሂደት ክፍተቶችን ለመሙላት እና ለቀጣይ የሥራ ዘመን ግብዓት እንደሚሆን አቋም ይዘናል።

አጀንዳ አራት: ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ምን ይመስላል? ምን መምሰል
አለበት? የፓርቲዎች ቁመና።

በዚህ አጀንዳ ስር ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉበትን ሁኔታ ገምግሟል። ይሄንን መሰረት አድርጎም እንዴት እና በምን ሁኔታ አብረን መስራት አንችላለን የሚለው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በዋናነትም ከሁሉም ድርጅቶች ጋር በሀገር አንድነት፣ በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባት እና የዜጎች በሰላም መኖር ላይ አብረን መሥራት ይገባል የሚል መግባባት ላይ ተደርሷል። እንዲሁም ኢዜማ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ክፍት መሆኑን ግልጽ ማድረግ እንደሚገባ እና ተነሳሽነት ወስዶ ሊሠራበት አንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፤ ይህንንም ለማስፈጸም 5 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል።

አጀንዳ አምስት: የሚነሱ ችግሮችን የምንፈታበት መንገድ ምን ይምሰል?

በዚህ አጀንዳ ስር በፓርቲያችን ወስጥም ሆነ ፓርቲው ከሌሎች አካለት ጋር በሚኖረው መስተጋብር ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችን የመፍቻ መንገድ ምን ሊሆን እንደሚገባ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በተለይ በፓርቲያችን ውስጥ የውይይት እና አብሮ የመሥራት ባህል ልምድ ሊዳብር እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን። በተለይ ከሌሎች አካለት ጋር በሚኖር መስተጋብር ለሚፈጠሩ ግጭቶች የመፍትሄው መንገድ ውይይት አና በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሊሆኑ አንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል። ሌላው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ጠንካራ እንዲሆን እና የፓርቲዎች የቃልኪዳን ሰነድ ተግባራዊነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል። በምርጫ ወረዳ አባላት ላይ ለሚደርስ ችግርን ከማዕከል ብቻ እንዲፈታ ከመጠበቅ ወረዳዎች በራሳቸው ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ የማብቃት ሥራ መሥራትም እንደሚገባን ተስማመተናል።

በአጠቃላይ ባደረግነው የአንድ ዓመት ፍተሻ ያሉብንን ድክመቶች በመለየት እና ጠንካራ ጎኖቹን በማጎልበት፣ መርህ መሰረት አድርጎ የፓርቲያችን የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ሰነድ ባስቀመጠው መሰረት በቀጣይ ለሚደረገው ምርጫ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ፤ በሁሉም አደረጃጀቶች የፓርቲው እንቅስቃሴ በእውቀት ላይ ተመስርቶ የፖሊስ አማራጮችን በማቅረብ እና ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ መሥራት መሆን እንዳለበት በመረዳት ዜጎች በተለይ የኢዜማ አባላት በአካባቢያቸው ሠላም እና ደህንነት ከሁሉም አካላት ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም

LEAVE A REPLY