ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለ14ኛ ዙር በወታደራዊ አመራርነት ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች ማስመረቁ ተሰምቷል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ ተመራቂዎች የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና የህዝባቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ወታደራዊ አመራሮች በዕውቀት ላይ ተመስርተው፣ ሀገርን እና ህዝብን ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የአቅም ግንባታ ግብ በሁሉም አውዶች መፋለም የሚችል ጠንካራ ኃይል መገንባት መሆኑን የገለጹት የኮሌጁ ኮማንዳንት ብርጋዴር ጀነራል ዳኛቸው ይትባረክ ፤ ዛሬ በከፍተኛ ስልታዊ አመራር 90 ሠልጣኞች መመረቃቸውን ጠቁመው፤ 18ቱ ከአምስት የጎረቤት ሀገር የመጡ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የመከላከያ ኅብረት ሥልጠና ዋና መምሪያ ሓላፊ ሌተናል ጀነራል ሀሰን ኢብራሂምን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸው ታውቋል።