ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– መነሻውን ከየመን በሶማሌ ላንድ አድርጎ ወደ አፋር እና ሶማሌ ክልል የገባው የአንበጣ መንጋ ሊገኝ ከታቀደው ምርት 2 በመቶውን (3.5 ሚሊዮን ኩንታል) ምርት እንዳወደመ ተሰማ።
የአንበጣ መንጋው ከ70 እሰከ 100 ፐርሰንት ምርት ሊያጠፋ ይችል እንደነበር የጠቆሙት በግብርና ሚንስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ከበደ በተደረገው ርብርበብ የደረሰው ጉዳት አነስተኛ ሊሆን መቻሉን አስረድተዋል።
ሶማሌ እና አፋር ክልል ላይ የአንበጣ መንጋው የመከላከል ሥራ ሢሠራ ቢቆይም ከአፋር የተረፈው ወደ ወሎ እና ደቡብ ትግራይ ወጥቶ ማሳ ላይ ሠፊ ጉዳት አድርሷል። በተያያዘ ከሶማሌ ክልል በመነሳት ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ላይ ጉዳት አድርሶ እንደነበርም ታውቋል።
ቀደም ባሉት ወራት በተሠራው የመከላከል ሥራ ዓመቱን ሙሉ በግጦሽ እና ቁጥቋጦ እንጂ በሰብል ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ያሉት ሓላፊ፤ ሆኖም በግጦሽ እና ቁጥቋጦ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ቦታዎቹ ስለማያመቹ ማጥናት እንዳልተቻለም አስረድተዋል።
ሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአፋር እና በሶማሌ ክልል የመከላከል ሥራ ቢሠራም፣ ለመድረስ አስቸጋሪ ከሆኑ አካባቢዎች ላይ አንበጣው በመነሳት በምስራቅ ኦሮሚያ፣ ድሬዳዋ እንዲሁም በምዕራብ አማራ ወሎ፣ ቃሉና አርጎባ አካባቢዎች መጠነኛ የሆነ የምርት መቀነስ አድርሶ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
በሁለተኛው ዙር ህዳር እና ታህሳስ ላይ በምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል የተከሰተ ቢሆንም ሰብል በመሰብሰቡ ጉዳት ያላደረሰ ሲሆን፤ በበልግ ምርት ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ በዳሰነች፣ ኛንጋቶም፣ ኦሞ እና የኬንያ አቅራቢያ አካባቢዎች ቢከሰትም በበልግ ሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል ተችሏል።
በ2012 ዓ.ም የክረምት ወራት በአፋር እና በሶማሌ ላይ በሚገኙ ሠፊ አካባቢዎች፣ በአውሮፕላን የታጋዘ የአሰሳ እና መከላከል በሰው ኃይል እና በመኪና እየተሠራ መሆኑም ተነግሯል።