ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን (IFRS) ገቢራዊ የማድረግ እቅድ እስካሁን እንዳልተሳካ ተነገረ።
የፋይናንስ ሪፖርት አቅራቢ ተቋማት ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን ወይም IFRS ገቢራዊ እንዲያደርጉ በማሰብ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅን ካፀደቀች 5 ዓመታት ያለፋት ቢሆንም፤ እስካሁን ይህ ሀሳብ ገቢራዊ ሳይሆን መቆየቱን የፋይናንስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በቀጣዮቹ 3 ዓመታት የንግድ ባንኮች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች ከፍ ያሉ ኩባንያዎች፤ አንድ ወጥ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎችን ገቢራዊ እንዲያደርጉ መመሪያ ተሰጥቷል።
የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ዓለም ዐቀፍ ደረጃዎችን በጠበቀ አንድ ወጥ መልኩ ገቢራዊ መደረጉ በኢትዮጵያ የዘመነና የተቀላጠፈ የፋይናንስ ሥርዓት ለመተግበር ያስችላል ነው የተባለው።
ባንኮች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የጡረታ ከፋዮች እና ሌሎች ግዙፍ ኩባንያዎች ወጥነት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ እንዲኖራቸው ይደረጋል ያለው ሚኒስቴሩ፤ አሠራሩ በዚህ ዘመን በእጅጉ መለመድ አለበት ብሏል።
የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዳይሬክተር ጀነራል ወይዘሮ ሒክመት አብደላ፤ በኢትዮጵያ ወጥነት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ እንዲኖር፣ ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመደበኛ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ዓመታዊ ሽያጫቸው ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ተቋማት የተሟላ ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎችን ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል ያለው ሚኒስቴሩ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት በኢትዮጵያ ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ በጋራ ሢሠሩ እንደቆዮም ይፋ አድርጓል።