የክልሎች ጣጣ || ፕሮፍ. መስፍን ወልደ ማርያም

የክልሎች ጣጣ || ፕሮፍ. መስፍን ወልደ ማርያም

ወያኔ ክልሎችን አካለ ስንኩላን አድርጎ የፈጠረው ለብልሃቱ ነው፤ ዋናው ዓላማ ጎሣዎችን በማናከስ ዳኛ ሆኖ አናታቸው ላይ ለመቀመጥ ነበር፤ ይህንን ዓላማ ሳይጨብጡ የክልሎችን አወቃቀር መደገፍ ዋና ሳይችሉ ባሕር ውስጥ መግባት ነው፤ ተናግሬአለሁ ማለቱ ፋይዳ የለውም እንጂ የክልል ሀሳብ ጭንጋፍ መሆኑን ከተናገርሁ ልጆች ተወልደው አድገዋል፤ እውነት ይዘገያል እንጂ እንደጸሐይ ጊዜውን ጠብቆ ይወጣል፤ ተንኮልም ከስቶና መንምኖ መቆም የማይችልበት ጊዜ ይመጣል፡፡

ችግሩ እንደተራራ ውሀ ግልጽ ነው፤ ክልል ማለት የጎሣ ቤት ነው ከተባለ እያንዳንዱ ጎሣ ትልቅም ይሁን ትንሽ እንደትግሬ፣ እንደአማራ፣ እንደኦሮሞ፣ እንደሶማሌ፣ እንደአፋር፣ እንደአደሬ … ሌሎቹ ሁሉ የየራሳቸው አጥር ያለው ቤት ያስፈልጋቸዋል፤ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 8 ለጎሣዎች በሙሉ ሉዓላዊነት ሰጥቷቸዋል፤ በተጨማሪም አጥሩ ከአንቀጽ 39 ጋር የተያያዘ ነው፤ አጥሩ እርስበርሳቸው እንዳይፋጁም ይረዳል፤ዛሬ ጎሣዎች ለክልልነት እንደሚጮሁት ነገ ደግሞ ለመገንጠል ይጮሃሉ! ስለዚህ አሁኑኑ አጥሩን በውል እያጠሩ ከልሎ አንቀጽ 39 ላይ ሲደርሱ ጣጣ የለም፤ አጥራቸውን ይዘው ውልቅ! የወያኔ ሕገ መንግሥትን ይዞ ለጎሣዎች ሁሉ የክልል ደረጃ መስጠት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ይሆናል፡፡

በአመራር ደረጃ ቆራጥነት ጠፋ፤ ዶር. ዓቢይ መለስ ዜናዊ ባነጠፈለት ኮረኮንች መንገድ ላይ ሳይጨነቅ እየተጓዘ ነው፤ ጠጠሮችን በመልቀም ኮረኮንቹን መንገድ ለማለስለስ መሞከር የሚያዋጣ አይመስለኝም፤ የላይቢሪያዋ የቀድሞ መሪ ዶር. ዓቢይ የሰላም ሽልማቱን ሲቀበል አንድ ነገር ብላ ነበር፤ የቆራጥነት ማጣት ችግር እንደሚፈጥርበት ተናግራ ነበር፤ ምን እንዳስመለከታት አላውቅም፡፡

የወያኔን ሕገ መንግሥት በመደረት ማሻሻል የሚቻል አይመስለኝም፤ በድሪቶ አገርን መምራት በጣም ያስቸግራል፤ ድሪቶ የደሀነት አርማ ነው፤ የሀሳብ ደሀነት ሕገ መንግሥቱን ድሪቶ ያደርገዋል፡፡ ይህ ድሪቶ ለዓቢይ አህመድ የሚስማማው አይመስለኝም፤

LEAVE A REPLY