ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጤናዬ አሳሳቢ ደረጀ ላይ ይገኛል በሚል እየተከራከሩ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው በቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ለአራተኛ ጊዜ ቀርበው ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገባቸው።
የከተማው የወረዳ ፍርድ ቤት በአንጻሩ መርማሪ ለፖሊስ ለምርመራ ተጨማሪ ሠባት ቀናት ፈቅዶለታል።
አነጋጋሪው ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው በተጠረጠሩበት ኹከትን በቢሾፍቱ ከተማ የማስነሳት ክስ ምርመራ ሲደረግባቸው መቆየቱ አይዘነጋም።
መርማሪ ፖሊስ በግለሰቡ እጅ ላይ የተገኘ የሽግግር መንግሥት መመስረቻ ሰነዶች ፣ የስልክ ልውውጥ እና ሲዲ ለምርመራ መላኩን ዛሬ ለችሎቱ ገልፆ ፤ አጠቃላይ የምስክር ቃል ለመቀበል እና የእነዚህ የምርመራ ውጤት ለማምጣት 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።
“ከዚህ በፊት አምስት ጊዜ ታስሬ ማስረጃ ስለሌለ ፍርድ ቤት ነው ነፃ ያደረገኝ፣ ለፍርድ ቤቱ ከፍ ያለ ክብር አለኝ፣ ነገር ግን አሁን ከሳሽ ብቻ ነው በተደጋጋሚ ጊዜ እየተሰጠው ያለው፣ ይህ ተገቢነት የለውም። እኔ የሕክምና ማስረጃ አምጥቼ ለሕክምና ዋስትና ስጠይቅ ውድቅ መደረጉ የአንድ ወገን ብቻ እየተሰማ መሆኑን ያሳያል፤ አራት ጊዜ ዳኞች እየተቀያየራችሁ ነው፣ መርማሪ ፖሊስ ተደጋጋሚ አንድ ዓይነት ምርመራ ነው እያቀረበ ያለው” በማለት አቶ ልደቱ ተቃውሞአቸውን በጠበቃቸው አማካይነት አሰምተዋል።
ለቀረቡት ክርክሮች የወረዳው ፍርድ ቤት፤ ” ችሎቱ የጊዜ ቀጠሮ ነው፣ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ጉዳይ ደግሞ በተረኛ ዳኛ የሚታይ እንጂ ሌላ ጉዳይ የለም፣ ፍርድ ቤቱ ገለልተኛና ሚዛናዊ ሆኖ ነው የሚመለከተው፣ በሚቀርበው የምርመራ ውጤት ልክ መዝኖ ነው ጊዜ የሚሰጠው፣ ይህ የፖለቲካ ጉዳይ የሚታይበትቦታ አይደለም” የሚል ምላሽ እንደሰጠ ታውቋል።
“ተጠርጠሪው ሕክምናውን በሀገር ውስጥ ማግኘት ይችላሉ ወደውጭ ቢወጡ በዚያው ሊቀሩ ይችላሉ” በማለት ጉዳዮን ከያዘው መርማሪ ፖሊስ ጋር አብሮ የተገኘው የቢሾፍቱ ከተማ ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ ሀሳቡን አስረድቷል።
የቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ መርማሪ ፖሊስ ቀረኝ ያለውን የምርመራ ውጤት አጠናቆ እና አካቶ እንዲቀርብ ተጨማሪ የሠባት ቀናት ጊዜ ፈቅዷል።