ከዐሥራ አንዱ የትግራይ ክልል የግል ተወዳዳሪዎች ሥድስቱ ከምርጫው ራሳቸውን አገለሉ

ከዐሥራ አንዱ የትግራይ ክልል የግል ተወዳዳሪዎች ሥድስቱ ከምርጫው ራሳቸውን አገለሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ህወሓት በደገሰው የትግራይ ክልል ምርጫ ለመወዳደር ከተመዘገቡ 11 የግል ተወዳዳሪዎች መካከል ሥድስቱ ግለሰቦች ራሳቸውን ከምርጫው አገለሉ።

የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ አቶ መረሳ ፀሐዬም ተወዳዳሪዎቹ ከሥድስተኛው ክልላዊ ምርጫ ውጭ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በክልሉ ከሚወዳደሩ የግል ተወዳዳሪ ፖለቲከኞች መሀል አንዱ የሆኑት አቶ አታክልቲ ገብረሥላሴ ከክልላዊው ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን ገልጸው፤ ለምርጫ ቅስቀሳ በመገናኛ ብዙኅን የአየር ሰዓት እንደሚያገኙና የምርጫ ኮሚሽን የሕትመት ወጪያቸውን እንደሚሸፍን አምነው ውድድሩን ተቀላቅለው የነበረ ቢሆንም ለጥያቄዎቻቸው ቀና ምላሽ ባለማግኘታቸው ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል እንደተገደዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሰው መሰብሰብና ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ መቀስቀስም አይቻልም። በመሆኑም በራድዮና በቴሌቭዥን መቀስቀስ ካልቻልኩ፣ ወጪዬ ተሸፍኖ በተለያዩ ቦታዎች ሐሳቤን የምገልጽባቸው መግለጫዎች ካልለጠፍኩ፣ እንዴት እቅዴን ለሰው አስተዋውቃለሁ?” በማለት የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽኑን አካሄድ የተቹት አቶ አታክልቲ ፤ የምርጫ ኮሚሽኑ ድጋፍ ሊሰጣቸው ፍቃደኛ ባለመሆኑ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለል ግድ እንደሆነባቸው አስታውቀዋል።
“የኛ ጥያቄ ብር ስጡን ሳይሆን ወጪያችንን ሸፍኑልንና አስፈላጊውን ግብዓት አሟሉልን ነው” ሲሉም ገንዘብ ከመፈለግ ጋር የተያያዘ ችግር አለመሆኑን ተወዳዳሪው ገልጸዋል።
ባለፉት ጊዜያት የመልካም አስተዳደር እጦትን፣ የመሬት አስተዳደርንና ሥራ አጥነትን በተመለከተ ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አተክልቲ፤ ችግሮቹ ሊፈቱ ባለመቻላቸው ቅሬታ ከማቅረብ በዘለለ ምክር ቤት ገብቼ የሕዝቡን ድምጽ ለማሰማትና ምክር ቤቱ መፍትኄ እንዲያስቀምጥ ለመታገል አስቤ ነበር በምርጫው የተመዘገብኩት ሲሉም እቅዳቸውን አብራርተዋል።
ከትግራይ ክልላዊ ምርጫ ራሳቸውን ካገለሉት መካከል ግማሹ በምርጫው በግል እጩነት ለመወዳደር የ1 ሺኅ ሰው የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ያልቻሉ ሲሆኑ፤ የተቀሩት በጀት ስላልተሰጣቸው፣ እንዲሁም የአየር ሰዐት ባለማግኘታቸው እንደሆነ ታውቋል።

LEAVE A REPLY