ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ቅድመ ምርመራ መዝገብ የዐቃቤ ሕግን የቃል ምስክር የሰማው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የእነጃዋርና የቤተሰብቻቸውን የባንክ አካውንት እንዲዘጋ አላዘዝኩም አለ።
ችሎቱ ምስክሮችን ከማድመጥ ባሻገር በቀደመው ቀጠሮ በተጠርጣሪዎች እና በዐቃቤ ሕግ ለተነሱ አቤቱታዎች ትዕዛዝ መስጠቱ ተሰምቷል።
በሽብርተኝነት የተከሰሱት ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ሲል ” ሚዲያዎች ከእኛ ፈቃድ ውጪ ፎቶ እያነሱን ነው፣ እንዲሁም ቪዲዮ እየቀረፁን ነው፤ ይህ እንዲቆም ትዕዛዝ ይሰጥልን” በማለት ላቀረቡት ጥያቄ፤
“ይህ ጉዳይ የተጠርጣሪዎችን ነጻ ሆኖ፣ የመታየት መብት የሚጋፋ ነው። ስለዚህም ሚዲያዎች የችሎቱን የዕለት ውሎ ከመዘገብ ውጪ ያለተጠርጣሪዎች ፈቃድ ፎቶ ማንሳትም ሆነ ቪዲዮ መቅረጽ አይችሉም” ሲል ፍርድ ቤቱ አዝዟል።
በተጨማሪም “ችሎት ውስጥ በብዛት እየታዩ እና እየታደሙ ያሉት የፌደራል ፖሊስ አባላት ናቸው፤ ስለዚህ ቤተሰቦቻችን ገብተው እንዲታደሙ ፈቃድ ይሰጠን” ሲሉ እነዚሁ ተጠርጣሪዎች ላቀረቡት ጥያቄ፤ ፍርድ ቤቱ ፖሊሶቹ በብዛት የሚገኙት ለደኅንነትና ለጥበቃ እንደሆነ ጠቁሞ፣ ከአራት ያልበለጡ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ችሎቱን እንዲታደሙ ለሚመለከተው አካል ትዕዛዝ እንደሰጠ ታውቋል።
በተመሳሳይ የኦ ኤም ኤን ጋዜጠኛ የሆነው ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ቤተሰቦቹን በስልክ ማግኘት እንዲችል ባቀረበው አቤቱታ መሠረት፤
ፍርድ ቤቱ በትናንት ውሎው ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ ቤተሰቦቹን በስልክ ማግኘት እንዲችል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች ባለፈው ችሎት ላይ” ዐቃቤ ሕጎች ስልክ ይዘው እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል። እኛ ግን እየተከለከልን ነው። ስለዚህ ሁለታችንም እንከልከል፣ አልያም ሁለታችንም ይፈቀድልን ” በማለት ላሰሙት አቤቱታ
ችሎቱ ሁለቱም አካላት ወደ ችሎቱ ስልክ ይዘው መግባት እንደማይችሉ በማሳወቅ ይህ እንዲተገበር ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ጃዋር መሐመድና በቀለ ገርባ የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው አካውንት በፍርድ ቤት ታግዷል ስለመባሉ ማብራሪያ በጠየቁት መሠረት ፍርድ ቤቱ እንደዚህ ዓይነት ትእዛዝ አለመስጠቱን ገልጾ ጉዳዮን እግዱን ከፈጸመው አካል ጋር መጨረስ እንደሚችሉ አስታውቋል።