ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጽንፈኛ ፖለቲካ አራማጆች የተፈጸመውን ወንጀል አስመልክቶ መንግሥት አዲስ አበባ ውስጥ ላሉ የብሪታኒያ ኤምባሲ ቅሬታውን አቀረበ።
ቅሬታው የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኩል በአዲስ አበባ ለሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ከፍተኛ ባለሥልጣን መሆኑ ተሰምቷል።
ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደጅ ላይ ከሰሞኑ ለተቃውሞ የተሰባሰቡት ሰልፈኞች የሃገሪቱን ባንዲራ በማውረድ የኦነግ አርማን መስቀላቸው መላ ኢትዮጵያውያንን ክፉኛ ማስቆጣቱ አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎ አምባሳደር ሬድዋን ኤምባሲው ላይ ስለተከሰተው ነገር በኢትዮጵያ የታላቋ ብሪታኒያና የዩናይትድ ኪንግደም ቻርጅ ዲ አፌር ለሆኑት አሌክስ ካሜሩን መንግሥታቸው የተሰማውን ቅሬታ ጠቁመው፤ ዩናይትድ ኪንግደም በዓለም ዐቀፍ ሕግ መሰረት የሃገሪቱን ኤምባሲና ሠራተኞች ከየትኛውም አይነት ጣልቃ ገብነት መጠበቅ እንዳለባትም አሳስበዋል።
አሳፋሪውን ድርጊት አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ የዩናይትድ ኪንግደም ቻርጅ ዲ አፌር አሌክስ ካሜሩን በኤምባሲው ላይ ስላጋጠመው ክስተት ይቅርታ መጠየቃቸውንና ሃገራቸው የኤምባሲውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ተገቢውን እርምጃ ትወስዳለች የሚል ማረጋገጫ መስጠቱንም ይፋ አድርጓል።
በወቅቱ ተቃዋሚዎቹ ለንደን በሚገኘው በኤምባሲው ደጅ ላይ በመሰባሰብ መንግሥትን የሚቃወም መፈክሮችን ሲያሰሙ ከቆዮ በኋላ፣ በኤምባሲው ህንጻ ላይ በመውጣት የአገሪቱን ባንዲራ አውርደው በሌላ መተካታቸው በተቀረፀ ምስል ላይ ታይቷል።