ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በበርካታ የቴሌቪዥንና የራዲዮ ተከታታይ ድራማ ድርሰቶቹ የሚታወቀው አድነው ወንድራድ (አዶኒስ) ሥርዓተ ቀብር ዛሬ በመንበረ ፅባኦት ካቴድራል (ሥላሴ) ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።
ተርጓሚ፣ የመድረክ ቲያትሮችና ተከታታይ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ድራማዎች ጸሐፊ የሆነው አዶኒስ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ በግርምትና በአድናቆት እጅን በአፍ የሚያስጭኑ በርካታ ሥራዎችን ቢሠራም ልታይ፣ ልታይ የማይልና ራሱን ሸሽጎ የኖረ የጥበብ ፈርጥ ነበር።
“አዶኒስ” ከሚለው የብዕር ስሙ ውጭ በድርሰትና የትርጉም ሥራዎቹ ላይ በመታወቂያ ስሙ ራሱን ገልጾ የማያውቀው አድነው ወንድይራድ ዓለም ላይ ከፍተኛ ተነባቢነት ያገኘው “የአና ማስታወሻ” መጽሐፍን ወደ አማርኛ በመተርጎም ከበርካታ ዓመታት በፊት ለንባብ አብቅቷል።
ይህንን የአና ማስታወሻ ታሪክን ወደ መድረክ ቴአትር በመቀየር በተለያዮ ቴአትር ቤቶች ለእይታ ከማብቃቱ ባሻገር “ክሊዮፓትራ” የተሰኘው የመድረክ ቴአትርን ጨምሮ በርካታ ተውኔቶችን ተርጉሟል፣ ጽፏል።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላልፈው ከፍተኛ ተወዳጅነት ያገኙት “ገመና” እና “መለከት” የተሰኙ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ለዓመታት የጻፈው አዶኒስ ባደረበት ሕመም በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ሕክምናውን ሲከታተል ቢቆይም ትናንት ሕይወቱ አልፏል።
ደራሲ አድነው ወንድይራድ (አዶኒስ) ከአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ በአርቴክት የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ተከታታይ የራዲዮ ድራማዎችና የመድረክ ተውኔቶች ጸሐፊ የሆነው የሀይሉ ጸጋዬ ወንድም ነው።
ኢትዮጵያ ነገ ባልደረቦች በደራሲ አዶኒስ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ ልባዊ መጽናትን ይመኛል።