67 ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዛሬ ይፋ አደረገች

67 ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዛሬ ይፋ አደረገች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና የኦሮሚኛ ሙዚቃ አቀንቃኙ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ ኦሮሚያ አካባቢዎች በክርስቲያኖች ላይ ደርሷል የተባለ ግፍና በደል አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የፓትሪያሪክ ጽ/ቤት መግለጫ አወጣ።

ዛሬ የወጣው መግለጫ በመንግሥት ባለስልጣናትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ግፍ የደረሰባቸው የሰማዕታትን መጠቃት ያለአግባብ ለቡድናዊና ፖለቲካዊ ትርፍ ከመጠቀም እና በሀዘናችን ከመሳለቅ ሊቆጠቡ ይገባል ሲል አሳስቧል።
ያለፈው ጥቃት ሳይበቃ አሁንም ዛቻና ማስፈራሪያ በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ በመሆኑ አጥፊዎቹን እንዲያስታግስ ቤተክርስቲያን ትጠይቃለች ሲሉ
መግለጫውን የሰጡት የመንበረ ባትሪያርክ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቡነ ያሬድ ፤  ቋሚ ሲኖዶሱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማፅናናትና መልሶም ለማቋቋም አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን በኦሮሚያ ክልል 6 አገረ ስብከቶችና 25 ወረዳዎች በአካል ተገኝቶ ተጎጂዎችንም አፅናንቶና ጥናትም አድርጎ መመለሱ ታውቋል።
ዐቢይ ኮሚቴው በመጀመሪያ ሪፖርቱ 67 ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ፣ 38 ያህሉ ከባድ፣ 29 ደግሞ ቀላል አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ከ7 ሺኅ በላይ ምዕመናን ተፈናቅለው በየቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢና በየግለሰቦች ቤት ተጠልለው ይገኛሉ ያለው መግለጫ፤ የምዕመናኑ ሀብት ገሚሱ መዘረፉን፣ ቀሪው ደግሞ መቃጠሉን አስታውቋል።
የፓትርያርኩ ጽ/ቤት አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰማዕታቱን መጠቃት ያለአግባብ ለፖለቲካዊ  ትርፍ ከማዋል እንዲቆጠቡ ጠቁሞ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች አብዝቶ እንደሚነገረው በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይሆኑ የተሳሳቱ ርዕዮተ ዓለማዊ ትርክቶችና ጂኦ ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረና እንዲሁም በተደራጀ መልክ የሚፈፀሙ ኦርቶዶክሲያውያንን የማፅዳት ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ብሏል።

LEAVE A REPLY