ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን ለሥድስተኛው የክልሉ ምርጫ 2.6 ሚሊዮን ሕዝብ መመዝገቡን አስታወቀ።
በክልሉ የሚካሄደው መደበኛው የመራጮች ምዝገባ ዛሬ የሚጠናቀቅ ቢሆንም፤ በተለያየ ምክንያት መመዝገብ ያልቻሉ ሰዎች ቅዳሜና እሁድ መመዝገብ እንዲችሉ ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቷል።
እስከ ነሃሴ 21/2012 (ዛሬ) ባለው ጊዜ ድረስ 2.6 ሚሊዮን መራጮች መመዝግባቸውን የገለጹት ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም፤ ይህም በትግራይ ክልል ታሪክ ትልቁ የመራጮች ቁጥር ነው ሲሉ አስተያየት ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነር በከፍተኛ ሁኔታ በትግራይ ውስጥ ሕዝቡ ለመራጭነት መመዝገቡን ይናገሩ እንጂ ህወሓት በባህሪዬው ሀሰተኛ ቁጥር ወዳድ በመሆኑና የተጋነኑ የቁጥር መረጃዎችን ለ27 ዓመታት በመጥራት ሕዝብን ሲዋሽ ከመኖሩ አኳያ ይህ የምዝገባ ቁጥርም ከእውነት የራቀ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው።
ኮሚሽኑ ምርጫውን እንዲታዘቡ በሚል ለሃገር ውስጥና ለዓለም ዐቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ጥሪ ማቅረቡንም ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ለድምፅ መስጫ የሚሆኑ 2 ሺኅ የምርጫ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ገዥው ፓርቲ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን ጨምሮ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቀናት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ በመነገር ላይ ነው።