ኢዜማ የመሬት ወረራውን በማስረጃ ለማጋለጥ የጠራበት ጋዜጣዊ መግለጫ ታገደ

ኢዜማ የመሬት ወረራውን በማስረጃ ለማጋለጥ የጠራበት ጋዜጣዊ መግለጫ ታገደ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አንዷለም አራጌ የሚመራው ኢዜማ በታከለ ኡማ አስተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጸመውን የመሬት ወረራና የኮንዶሚኒየም እደላን በተመለከተ ዛሬ ሊሰጠው የነበረው መግለጫ በፖሊስ ታገደ።
በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚንጸባረቁ የተረኝነት እንቅስቃሴዎችንና ፖለቲካዊ ጉዳይችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ የሚታወቀው የባልደራስን ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ሲከለክል የከረመው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬም ይህንን የአፋኝነት ተግባሩን በኢዜማ ላይ ደግሞታል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ዛሬ ነሐሴ 22/2012 በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሔዱ የመሬት ወረራዎችን እና ኢ-ፍትሀዊ የሆነ የመኖሪያ ቤቶችን ክፍፍል በሚመለከት በራስ ሆቴል አዳራሽ ሊሰጥ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመዘገብ በርካታ የሚዲያ ተቋሞች በቦታው ተገኝተው ነበር።
ይሁን እንጂ ከበላይ አለቆቻቸው ጥብቅ መመሪያ የተሰጣቸው መሆኑን የገለጹ በርካታ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በስፍራው የነበሩትን ጋዜጠኞች በማባረር፤ ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲበተን አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ጉዳዮን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡት ያነጋገርናቸው የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃፈሓላፊ ናትናኤል ፈለቀ ጋዜጣዊ መግለጫው በመንግሥት አካላት ዘንድ እውቅና እያለው በፖሊስ መከልከሉን ተናግረዋል።
“ከቀናት በፊት ስለ ስብሰባው ወይም ጋዜጣዊ መግለጫው ለሰላም ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ሁሉ በደብዳቤ አሳውቀናል” ያሉት የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ፤ በዚህ መሠረት ዛሬ ነሐሴ 22/2012 ዓ.ም ኢዜማ በራስ ሆቴል ሊሰጥ የነበረው  መግለጫ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ “ስለ መግለጫው መረጃ የለኝም ” በሚል መግለጫው እንዳይካሔድ ከልክሏል ብለዋል።
በታከለ ኡማ የሥልጣን ዘመን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የባልደራሱን መግለጫ፤ መግለጫው በሚሰጥበት አካባቢ ባለ ወረዳ ወይም ክ/ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት  ካስከለከለ በኋላ ዘግየት ብሎ “የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫው እንዳይሰጥ አልከለከለም” በሚል ሲከራከር መቆየቱ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY