እነጃዋር መሐመድ ላይ ምስክርነት ለመስማት ለማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

እነጃዋር መሐመድ ላይ ምስክርነት ለመስማት ለማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

 ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤  ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በ14ቱም ተጠርጣሪዎች ላይ ቀሪ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለፊታችን ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ  ተሰማ።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጃዋርን ጨምሮ  ከአራተኛ እስከ 14ኛ  የተዘረዘሩ ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ነፃ መሆናቸውን የሚገልፅ ውጤት ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አቅርቧል።
ቀደም ሲል  ጃዋር መሀመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ከጓደኞቻችን ጋር መገናኘት አልቻልንም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ በጓደኛ የመጠየቅ  መብት ቢኖራቸውም፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚከለክል በመሆኑ ጥያቄያቸውን ለጊዜው ውድቅ አድርጎታል።
በተጨማሪም አንደኛ ተጠርጣሪ የሆነው ጃዋር “ከልጄ እና ከባለቤቴ ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንድገናኝ ይፈቀድልኝ ” ሲል ያቀረበው ጥያቄ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት በማግኘቱ በሳምንት ሁለት ጊዜ በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንዲገናኙ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ጆሮዬን ስለታመምኩ የተሻለ ሆስፒታል ልታከም ብለው አቤቱታ ያቀረቡት 12ኛ ተጠርጣሪ አቶ ሸምሰዲን ጣሃ በመረጡት ሆስፒታል እንዲታከሙ እንዲመቻችላቸው ትእዛዝ የሰጠው ችሎቱ፤ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ ቀሪ ምስክሮችን ለማድመጥ ለፊታችን ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ  ሰጥቷል።

LEAVE A REPLY