ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአስራት ሚዲያ ባለሙያዎች ላይ ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት፤ የአዲስ አበባ እስረኞች አስተዳደር ሓላፊ ቀርቦ በተጠርጣሪዎቹ የጤና ሁኔታ እና የእስር አያያዝ ላይ ማብራሪያ መስጠቱ ተሰማ።
እስረኞቹ የኮቪድ 19 ምርመራ እንደተደረገላቸው እና ነፃ መሆናቸውን ፖሊስ ያስታወቀ ቢሆንም፤ ተጠርጣሪዎቹ በፅዳት እጥረት ለጤና ችግር እየተጋለጥን ነው ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ “ተጠርጣሪዎቹ ከዐሥር ሲፈቱ በጤናቸው ላይ እክል አጋጥሞ ጠባሳ ይዘው መውጣት የለባቸውም፣ ፖሊስ ትእዛዝ እስከሚሰጠው ድረስ መጠበቅ የለበትም፣ ደህንነታቸው እና ጤንነታቸው በተጠበቀ ቦታ ሊቆዩ ይገባል” ሲል ጠበቅ ያለ ትእዛዝ መስጠቱ ተሰምቷል።
በዚህ መሠረት ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲመጣ ችሎቱ ተጨማሪ ሠባት የምርመራ ቀናት እንደፈቀደ ለማወቅ ተችሏል።
አሥራት ሚዲያ በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሥርጭቱን ለማቆም ቢገደድም፤ የተቋሙ ሁለት ጋዜጠኞችና አንድ ካሜራ ማን ከሳምንታት በፊት ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው ለእስር ተዳርገዋል።
በወቅቱ ፖሊስ የአሥራት ማዲያ ጋዜጠኞችን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሲያስራቸው በጣቢያው ላይ ከህዳር ወር እስከ ሰኔ ወር የአማራን ሕዝብ ለአመፅ የሚያነሳሳ ፕሮግራምችን ስታቀርቡ ነበር እንዳላቸው እስረኞቹ የሚዲያ ባለሙያዎች መናገራቸው አይዘነጋም።