ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በአቶ ጃዋር ሞሐመድና ሌሎች 13 ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ በተመለከተበት የዛሬው ችሎት በፌዴራል ፖሊስ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስረኞች አስተዳደር ሓላፊ በፖሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱ ታወቀ።
ፍርድ ቤቱ ሓላፊው በ24 ሰዐታት ውስጥ ታስረው እንዲቀርቡ ነው ትዕዛዝ ያስተላለፈው። በእነ ጃዋር ሞሐመድ የክስ መዝገብ ውስጥ ያሉት የኦኤምኤን ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳና ሌሎች አራት ሰዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤት እንዲያመጡ የተሰጠው ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ተፈፃሚ ባለመደረጉ ነው ይህ ትዕዛዝ ከችሎቱ የተሰጠው።
ነሐሴ 20/2012 በነበረው ችሎት ላይ ተጠርጣሪዎቹ ለምን የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዳልተደረገላቸው ኃላፊው ፍርድ ቤት መጥተው እንዲያስረዱ ቢያዝም፤ አስተዳዳሪው ዛሬ በነበረው ችሎት ላይ ካለመቅረባቸው ባሻገር፤ ተወካይም ሳይልኩ ቀርተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጃዋር ጠባቂዎች የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ ከተራ ቁጥር 4-14 የተዘረዘሩ ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ነፃ መሆናቸውን የሚገልፅ ውጤት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት ልኳል።
ይሁን እንጂ ከተራ ቁጥር 4 እስከ 9 ያሉ ተጠርጣሪዎች ከኮቪድ-19 ነፃ መሆናቸው ቢረጋገጥም ዛሬ ፍርድ ቤት ባለማቅረባቸው ተይዞ የነበረው የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን የመስማት ሂደት ለሰኞ ቀጠሮ ተይዞለታል።