ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከ25 ቀናት በኋላ የሚከበረው የመስቀል በዓል የደመራ ሥነ ሥርዓት የሚከናወንበት ታሪካዊው መስቀል አደባባይ ዓለም ዐቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ገንብቶ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ተባለ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመስቀል አደባባይን ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ላይ፤ ‘ባለፉት ጥቂት ወራት በመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ያለ መታከት ሲደክሙ በቆዩት ወገኖች እጅግ ተደንቄያለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
በመስቀል አደባባይ ማስዋብ ፕሮጀክት በዚህኛው ዙር በአጠቃላይ 5 ሺኅ ያህል ሠራተኞች እየተሳተፉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ታሪካዊ አደባባይ ዓለም ዐቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ከሦስት ሳምንታት በኋላ በመስከረም 2013 ዓ.ም አጋማሽ በኦሮቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል በዓል ዋዜማ በስፍራው የሚካሄደው የደመራ ሥነ ሥርዓትን ለማክበር እንዲያስችል ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የውስጥ መመሪያ መተላለፉን ታማኝ ምንጮች በመናገር ላይ ናቸው።