የተቋረጡ የስፖርት ውድድሮችን ለመጀመር የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ

የተቋረጡ የስፖርት ውድድሮችን ለመጀመር የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን መልሶ ለማስጀመር የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቷል ተባለ።

በሀገሪቱ የወረርሽኙ ስጋት ባለበት ሁኔታ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መልሰው እንዲጀመሩ ለማድረግ በተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይትና ምክክር በመካሄድ ላይ ነው።
 የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ኤሊያስ ሽኩር  በበሽታው ምክንያት የተቋረጡትን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከዚህ በላይ እንዲዘገዩ ማድረግ በስፖርት ቤተሰቡ ላይ የሚፈጠረው ጫና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
 የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ሲባል በሃገሪቱ ስፖርታዊ ስልጠናዎች፣ ውድድሮች በአጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ከተደረገ መሰነባበቱን ተከትሎ
የስፖርት ዘርፉ ክፉኛ መጎዳቱን ያመለከተው ኮሚሽኑ፤ ክለቦች የመፍረስ አዳጋ እንደተጋረጠባቸውና የስፖርት ቤተሰቡም የሥነ ልቦና እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን ይፋ አድርጓል።
ከዚህ በመነሳት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ረቂቅ መመሪያው ተዘጋጅቶ ውይይት እንደተካሄደበት ታውቋል።
የወጣው መመሪያ አጠቃላይ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በምን ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው የሚያሳይ ከመሆኑ ባሻገር፤ የስፖርት ተቋማትና ማኅበራት ከሚያካሂዷቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ባህሪ አንጻር አስፈላጊ የጥንቃቄና የአሠራር ሥርዓት ሊያዘጋጁ እንደሚችሉ እንደሚደረግም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎ የስልጠናና የውድድር ስፍራዎች ለበሽታው ያላቸውን ተጋላጭነት ባገናዘበ ሁኔታ ደረጃ በደረጃ በግልና በቡድን አነስተኛ ተሳታፊ ቁጥርን ታሳቢ ያደረገ  ውድድሮች ሊዘጋጁ እንደሚገባ ተነግሯል።
ወደ ስልጠናና ወድድር የሚገቡ አካላት ምርመራ ማድረግ፣ የንጽህና መጠበቂያዎችን መጠቀምና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያገለግሉ ቦታዎች፣ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎች ንጽህናቸው ሊጠበቅ እንደሚገባም ከመመሪያው መረዳት ተችሏል።

LEAVE A REPLY