ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢዜማ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሰጠው መግለጫና በተለያዮ መንገዶች፣ የመረጃ ማሰባሰቢያ ዜዴዎች አማካይነት አገኘሁት ባለው ተጨባጭ ውጤት መሠረት ታይቶ በማይታወቅ መጠንና ስፋት ግልፅ የሆነ የመሬት ወረራ እና ሕገ-ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ በዋና መዲናዋ መከናወኑን ይፋ አደረገ።
በህገ ወጥ መንገድ የተያዙት እነዚህ ቦታዎች ሕጋዊ ይዘት እንዲኖራቸው የሚያስፈልጋቸው ሰነዶች እንደተዘጋጁላቸው ደርሼበታለሁ ያለው ኢዜማ፤ የከተማው አስተዳደር አካላትም ይህን ሂደት ጠንቅቀው ያውቃሉ ሲል የታከለ ኡማ አስተዳደር የህገወጥ መሬት ወረራውና የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላው ተባባሪ እንደነበር አጋልጧል።
“የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገ-ወጥና በተደራጀ መልኩ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታና ፕላን ተሠርቶላቸው ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ ተላልፈዋል በማኅበርና በግል ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርገዋል” ያለው የዛሬው የኢዜማ መግለጫ ፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተም የከተማው አስተዳደር ባወጣው ደንብ መሰረት በምንም መስፈር የቤት ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤትና የነዋሪነት መታወቂያ ተሰጥቷቸዋል ብሏል።
ሠፊ ጊዜ የወሰደው የኢዜማ ጥናት በከተማዋ የተለያየ ዓይነት ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ከማመላከቱ ባሻገር፤ በጅምር ቤት ስም ከባለ ይዞታዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በመግዛት ግንባታ የማካሔድ፣ ባዶ መሬቶችን በቡድንና በግለሰብ ደረጃ በማጠር የመያዝ እንዲሁም ለሌላ ወገን ማስተላለፍ ይገኙበታል ሲል ገልጿል።
በተጨማሪም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተዘረጋው ሰንሰለት በጥቅም ተጋሪነትና በዝምድና ሠፋፊና ቁልፍ ቦታዎችን መያዝ ባለፉት ሁለት ዓመታት በከተማዋ ውስጥ መታየቱንም አረጋግጧል።
በመሬት ወረራው ላይ ግንባር ተሳታፊ የነበሩት ሰዎች “ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን ናቸው፤ በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል” የሚሉ ግለሰቦች፣ እንዲሁም ወረራ የተፈፀመባቸው አካባቢ ላይ የሚገኙ የክፍለ ከተማና የወረዳ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች እንደሆኑ ተሰምቷል።
የተፈፀመው የመሬት ወረራ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮች የተሳተፉበት እንደሆነ ያጋለጠው ኢዜማ፤ ሓላፊዎቹ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አደረጃጀቶች መሬቱን ወረው እንዲይዙ አመቻችተዋል፤ የመንግሥትን ሥልጣንንም ለሕገ ወጥ ተግባር ከለላ እና ሽፋን እንዲሆን አድርገዋል ሲል ከሷል።