የአዋሽ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት አቋረጠ፣ አዋሽ 2 ደግሞ በእንቦጭ...

የአዋሽ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት አቋረጠ፣ አዋሽ 2 ደግሞ በእንቦጭ ምክንያት ተዘጋ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና በአዋሽ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ ማጋጠሙን ተከትሎ ከቅዳሜ ነሐሴ 23፣2012 ጀምሮ ጣቢያው ለጊዜው አገልግሎት ማቋረጡ ተሰማ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፤ የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲሳሳ ገልሜሳ በአዋሽ ወንዝ ላይ እየተከሰተ ያለው ጎርፍ እና የእንቦጭ አረም በቆቃ፣ በአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ትልቅ ሥጋት ፈጥሯል ብለዋል።
በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ ከቆቃ ግድብ ከሐምሌ 15፣2012 ጀምሮ በሰከንድ 60 ሜትር ኪዩብ ውኃ ሲለቀቅ ቢቆይም፤ ወደ ግድቡ የሚገባው የውሃ መጠን በየጊዜው እየጨመረ በመሆኑ፣ ከግድቡ የሚለቀቀው የውሃ መጠን አሁን ላይ በሰከንድ 625 ሜትር ኪዩብ ውሃ መድረሱን ተሰምቷል።
 49 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውና 32 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የአዋሽ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በውሃ መጥለቅለቅ አደጋ ሳቢያ አሁን ላይ ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት መስጠቱን ማቆሙን ሓላፊው አስረድተዋል።
በተያያዘ ዜና የአዋሽ 2 የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ደግሞ የውሃ መቀበያው በእንቦጭ አረም በመዘጋቱ ከሐምሌ 23 2012 ጀምሮ አገልግሎቱ የተቋረጠ ሲሆን፣ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት አረሙን በኤክስካቫተር የማንሳት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋ አድርጓል።

LEAVE A REPLY