ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች በድጋሚ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየታደላቸው መሆኑን ኢዜማ በማስረጃ ማረጋገጡን ገለጸ።
ከአሁን ቀደም በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ቦታ እና ኮንዶሚኒየም ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሠራተኞች የተሰጣቸው መሆኑን ያስታወሰው ኢዜማ በአሁኑ ወቅት በድጋሚ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየታደላቸው መሆኑን በማስረጃ ኤጋግጫለሁ ብሏል።
ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች ሳር ቤት አካባቢ ከሚገኘው ጽሕፈት ቤት፤ ሁሉም የተመዘገቡ ሠራተኞች በሰኔ 12/2012 በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች የድልደላ እጣ የወጣላቸው ሲሆን፣ የድልድል እጣ ለደረሳቸው ሰዎች ሰኔ 16/2012 ድልድል መደረጉን ኢዜማ አጋልጧል።
በተጠቀሰውቀን ሁሉም ሠራተኞች የኮንዶሚኒየም ብሎክ ቁጥር እና የቤቱ ቁጥር በስማቸው ተረጋግጦ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በተሰጣቸው የቤት ቁጥር የነዋሪነት መታወቂያ የተዘጋጀላቸው መሆኑን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜሜ)፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን (ኮንዶሚኒየም) ሕገ ወጥ እደላ በተመለከተም ድርጊቱን የመንግሥት ሕገ ወጥ ተግባር ነው ሲል ወቀሳውን በሥርዓቱ ላይ አድርጓል።
በኮየ ፈጬ እና በሌሎች ሳይቶች የተሰራው ኢፍትሃዊ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥና አጠቃቀም ከመመሪያ ጀምሮ ችግር እንዳለበት የገለጸው ፓርቲው፤ የአስተዳደሩ ቤቶች ልማት ቢሮ የጋራ መኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ወጥቶ የጸደቀውን መመሪያ ቁጥር 3/2011 ሰኔ 2011 እና ከመመሪያው ቀድሞ የካቲት 27/ 2011 ዕጣው ለሕዝብ የተገለፀውን ተግባር ላይ ሳይውል መቀየቱንም አስታውቋል።
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፕሮጀክቶች አፈጻጸምን ከፍተኛ ድክመት እና ለተንሰራፋው ሙስና ዋና ማሳያ የሚሆነው መስከረም 2012 ፣ 5 ሺኅ ቤቶችን ለግንባታ አቅዶ በበጀት ዓመቱ ምንም የተገነባ እና የተጀመረ ቤት አለመገኘቱንም በማስረጃነት የጠቀሰው ኢዜማ፤ ይህን ለማስፈጸም በኦሮሚያ ክልል ጽሕፈት ቤት በኩል ኮሚቴ ተቋቁሞ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች መታወቂያ የተሠራላቸው መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች መረጃዎች መገኘቱንም አብራርቷል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንጻዎች ውስጥ የተሠሩ የንግድ ቤቶችን በተመለከተ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች፣ ልጅ እና የልጅ ልጅ ተብለው በገፍ ስለመታደላቸው፤ በእግር ኳስ ደጋፊነት ስም ለተሰባሰቡ ማኅበራት መከፋፈላቸውን ጭምር የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃዎች ተገኝተዋል ነው የተባለው፡፡