ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በግል ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች የምዝገባ እና የትምህርት ክፍያ ላይ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ክፍያ እንደማይደረግ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶቹ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ መመሪያ ቢያወጣም ሰሞኑን ምዝገባ የጀመሩ አብዛኛው ትምህርት ቤቶች የስድስት እና የሦስት ወር ክፍያ እንዲፈጽሙ ከማስገደዳቸው ባሻገር የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማቅረብ ወላጆችን እያስጨነቁ ይገኛሉ።
የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ምዝገባ ከነሀሴ 20 ጀምሮ እንዲከናወን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁን ተከትሎ ከተማሪዎች ምዝገባ እና ከትምህርት ክፍያ ጋር ተያይዞ ወላጆች በተለያዮ ሚዲያዎች ላይ ቅሬታቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።
በዚህ መነሻ መሠረት ትምህርት ሚኒስቴር፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ተቋሙ ያወጣውን የትምህርት ቤት ምዝገባ ክፍያ መመሪያን ተላልፈው ምዝገባ እያከናወኑ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና ከመመሪያ ውጪ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለወላጆች ተመላሽ እንዲያደርጉ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
በቀጣዮ የትምህርት ዘመን ምዝገባ ላይ ምንም ዓይነት የክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደማይቻል እና እንደሚያስጠይቅም ነው የትምህርት ሚኒስቴር የገለጸው።
ትምህርት ቤቶችም ምዝገባ ሲያካሂዱ ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት የነበረውን የክፍያ አቀባበል ዘዴ መቀየር የማይችሉ መሆኑን እና ከዚህ በፊት በነበረው የክፍያ ስርዓት መቀጠል እንዳለባቸው የገለጸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ፤ ከዚህ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ የትምህርት ክፍያ እና ከመመዝገቢያ ክፍያ ውጪ ሌሎች ተጨማሪ ክፍያ ማስከፈል አይችሉም ብሏል።