በአፋር ክልል በጎርፉ ምክንያት 120 ሺኅ ሰዎች ለኮሮና አስጊ በሆነ መጠለያ ውስጥ...

በአፋር ክልል በጎርፉ ምክንያት 120 ሺኅ ሰዎች ለኮሮና አስጊ በሆነ መጠለያ ውስጥ ናቸው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና በአፋር ክልል በሚገኙ 14 ወረዳዎች ውስጥ ከ120 ሺኅ በላይ ሰዎች በጎርፉ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል ተባለ።

የክልሉ የአደጋ መከላከል ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ኃላፊ አቶ ማሂ አሊ፤ በአሳይታ፣ አፋምቦ፣ ዱብቲ እና ዞን 3 አካባቢዎች ለተፈናቀሉት ሰዎች ከፌደራል መንግሥት፣ ከክልሎች እና ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተገኙ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በጎርፍ አደጋው እስካሁን የሰው ሕይወት አለመጥፋቱን የገለጹት ሓላፊው ፤  ሰዎች በጎርፉ ከቤታቸው ሲፈናቀሉ ምግብና መገልገያ ቁሳቁሶችን ባለመያዛቸው ለችግር ተጋልጠዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ጎርፉ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ጥጥ፣ በቆሎን ጨምሮች ከ 21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የነበሩ የደረሱ ሰብሎችን ከጥቅም ውጭ አድርጓል።
ገለአሎ ወረዳ ላይ “ደበል” እና “ገፍረሞ” በተሰኙ ቀበሌዎች በውሃ የተከበቡ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ማሂ ሰዎቹን ከአካባቢዎቹ ለማውጣት ጀልባ እና ሄሊኮፕተር ከመከላከያ ተጠይቆ እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል።
 አዋሽ ፈንታሌ፣ ገዋኔ፣ ገልአሎ፣ አሚበራ እና ዱለቻ በሚባሉ አካባቢዎች ከቆቃ እና ቀሰም ግድቦች በሚለቀቀው ውሃ፣ አሁንም በአካባቢው እና በሌሎች አካባቢዎች እየጣለ ባለው ዝናብ ምክንያት ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት መኖሩ ታውቋል።
በጎርፉ የተፈናቀሉ ሰዎች በ14 ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ሲሆን፤ በጣቢያዎቹ ጥግግት ቢኖርም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የህክምና ባለሙያዎች እና በጎ ፈቃደኞች ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።

LEAVE A REPLY