አሜሪካ ገንዘቡን ማገዷ በዲፕሎማሲም፣ በሞራልም አግባብነት የለውም ሲሉ ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ

አሜሪካ ገንዘቡን ማገዷ በዲፕሎማሲም፣ በሞራልም አግባብነት የለውም ሲሉ ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ አማካይነት ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የገለጸችው ጉዳይ በሞራልም፣ በዲፕሎማሲም አግባብነት የሌለው መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ተናገሩ።

” አሜሪካ በየዓመቱ ለኢትዮጵያ በተገባው ውለታ መሰረት ለአንዳንድ አስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች የምታደርገውን ፈሰስ ለማቋረጥ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል መግለጫ ሰጥታለች። አሜሪካ የምታደርገው የገንዘብ ወጪ የሚውለው ለኢትዮጵያም ለአሜሪካም የጋራ ጥቅም ነው። በተለይም በአካባቢ ደህንነት ሁለቱ አገሮች የሚተባበሩበት የቆየ አይነት ስምምነትና አሠራር ላይ የሚውል ገንዘብ በመሆኑ የገንዘብ ፈሰሱን አቋርጣለሁ ማለቷ በሞራልም በዲፕሎማሲም አግባብነትም ተቀባይነትም የሌለው ነው”
ያሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፤ የአሜሪካ አስተዳደር የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ካለፈው ጥቅምት እና ህዳር ወር ጀምሮ አግባብ ባለው መግባባት ጉዳያችሁን በተመልካችነት ልይላችሁ ሲል መሰንበቱንም አስታውሰዋል።
 ስትወያዩ ተመልካች እሆናለሁ ማለት የተለመደና የጨዋነት እንዲሁም የወዳጅነት ሐሳብ ነው በሚል ሀሳቡን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስቱም ሃገራት ተቀብለው እስካለፈው የካቲት ወር ድረስ ሲወያዩ የነበረ ቢሆንም፤ ይሁንና አሜሪካ ቀስ በቀስ ውግንናዋን ወደግብጽ እያደረገች ስትመጣ ኢትዮጵያ ሁኔታው ሚዛኑን የሳተ መሆኑን በመረዳት ብሄራዊ ጥቅሟን አሳልፋ ላለመስጠት  ትክክለኛውን ውሳኔ መወሰኗን ተመራማሪው ፕሮፌሰር አብራርተዋል።
“በተለይ የግብጽን የቆየና ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ በፊርማ እንዲረጋገጥ አሜሪካ ግፊት ማድረጓ ስለተረጋገጠም ኢትዮጵያ ከውይይቱ የወጣችበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል” ያሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፤ በወቅቱ አሜሪካ ራሷን ከተመልካችነት ወደ አደራዳሪነት አሸጋግራ ሰነድ በማዘጋጀት ፈርሙ በማለት ልካ እንደነበርም ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY