ፓልም የምግብ ዘይት በቀጣዮ ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ መመረት ይጀምራል መባሉ እያነጋገረ ነው

ፓልም የምግብ ዘይት በቀጣዮ ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ መመረት ይጀምራል መባሉ እያነጋገረ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና ህወሓት መራሹ መንግሥት በገፍ ወደ ኢትዮጵያ ሲያስገባው የነበረውየፓልም የምግብ ዘይት ከቀጣይ ዓመት ጅምሮ በሃገር ውስጥ ሊመረት መሆኑ ተሰማ።

መንግስት ከውጪ የሚያስመጣው የፓልም የምግብ ዘይት ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በሃገር ውስጥ በከፊል ሊመረት መሆኑን ያሳወቀው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው።
መንግሥት በዜጎች ላይ የኑሮ ውድነት እንዳይፈጠር፣ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በድጎማ ከውጪ ከሚያስገባቸው ሸቀጦች ውስጥ አንዱ የሆነውን ፓልም የምግብ ዘይት ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በሃገር ውስጥ ለማምረት እንቅስቃሴ መጀመሩን ፤ በሚኒስቴር የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ትራንስፎርሜሽን ዳይሬከተር የሆኑት አድማሱ ይፍሩ አስረድተዋል።
ይህንንም ፌቬላ ኢንዱስትሪ ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ደብሊው ኤ የዘይት ማምረቻና ማከፋፈያ ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እና አል ኢምፔክስ ዘይት ማምረቻ የተባሉት አራት ፋብሪካዎች ዘይቱን ለማምረት ፍቃድ እንደተሰጣቸውም ተገልጿል።
ፓልም ዘይት በወያኔጨ/ኢህአዴግ ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ይገባ በነበረበት ሂደት ውስጥ በርካቶች ለጤና ችግር መጋለጣቸውና በለውጡ ማግስትም የንግድ ሚኒስቴር  ዘይቱ በሰዎች ጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ በመሆኑ ከእንግዲህ በኋላ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገባ ለመንግሥት በደብዳቤ አሳውቂያለሁ ማለቱ አይዘነጋም።
በዛው ሰሞን ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለው የፓልም ዘይት በአንድ ወቅት ግብፅ ለሳሙና ፋብሪካ ግብዓትነት በመርከብ አስጭና ወደ ሃገሯ ልታስገባ ባለችበት አጋጣሚ ምርቱ በጉዞ ላይ እያለ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ድርድር አድርገው ወደኢትዮጵያ  ገብቶ ለምግብነት እንዲውል መደረጉን አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ተናግረው ነበር።
ይህ ዘይት እንዲህ ዓይነት የላቀ ችግር ያለበት መሆኑ እየታወቀ ከቀጣዮ ዓመት ጀምሮ ድፍድፉን ከውጭ በማስገባት በኢትዮጵያ ለማምረት ዝግጅት መጀመሩ ፤ ዘይቱ በምን ዓይነት የጥራት ደረጃ ይመረታል? የሚል ጥያቄን በዜጎች ዘንድ ከወዲሁ ፈጥሯል።
የተጠቀሱት ኩባንያዎች የምርት ሂደታቸውን በቅርቡ እንደሚጀምሩ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ለግብዓትነት የሚጠቀሙበትን የዘይት ድፍድፍ ከውጪ ለማስመጣት ከብሄራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሬ ጥያቄ አቅርበው አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውንም ይፋ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY