ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ የተቀሰቀሰውን ሁከትና ብጥብጥ በማስተባበርና በገንዘብ በመርዳት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙት የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳያቸው በሚታይበት የቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ዛሬ አዲስ ውንጀላ ቀረበባቸው።
በዛሬው የፍርድ ቤቱ ውሎ ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ አቶ ልደቱ የሽግግር መንግሥት ስለሚመሠረትበት ሁኔታ በጽሑፍ ያዘጋጁትን ሰነድ፣ እንዲሁም “ለውጡ ከድጡ ወደማጡ ” የሚል ረቂቅ ጽሑፍ በብርበራ አግኝቼባቸዋለሁ የሚል አዲስ ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት ዛሬ ጠዋት በዋለው ችሎት ዐቃቤ ሕግና ፖሊስ በአቶ ልደቱ አያሌው ላይ አዲስ ያቀረቧቸውን ውንጀላዎች የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ቢጠይቅም፣ ዐቃቤ ህግና ፖሊስ ማስረጃውን ማቅረብ አለመቻላቸውን የአቶ ልደቱ ጠበቃ አቶ አብዱልጀባር ሁሴን ገመዳ አስታውቀዋል።
ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግና ፖሊስ በአቶ ልደቱ አያሌው ላይ ያቀረቡትን ውንጀላ የሚያስረዳ የምርመራ መዝገብ እንዲያቀርቡ ለከሰአት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ መሆኑን የገለጹት ጠበቃው፤ ፖሊስና የወረዳው ዐቃቤ ሕግ “መዝገቡን ለዞኑ ዐቃቤ ሕግ ልከነዋል ” በማለት ማቅረብ እንዳልቻሉም ይፋ አድርገዋል።
ይህንን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ፣ ፖሊስ የምርመራ መዝገብና ማስረጃውን እንዲያቀርብ በማዘዝ ለነገ ጠዋት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ችሎቱ በነገው ቀጠሮ ማስረጃውን አይቶ ከሰዐት በኋላ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በተያያዘ ዜና የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በፖሊስ ቁጥጥር ውለው የሰነበቱት አቶ ይልቃል ጌትነት ከሁለት ወር እስር በኋላ ዛሬ በዋስትና መፈታታቸው ታውቋል።
ከክስተቱ ጋር በተያያዘ ሰኔ 25፣2012 ምሽት በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት የኢትዮጵያውያን ሃገር ዐቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀ መንበር አቶ ይልቃል ጌትነት ከእስር መለቀቃቸውንም ፓርቲው አረጋግጧል።