ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሕብረተሰቡ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ መፈቀዱ ተሰማ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚነስቴር በገለጸው መሠረት መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ተብለው ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ የተፈቀደላቸው የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ የዳቦ ስንዴ፣ ሩዝ እና የሕጻናት ወተት መሆናቸው ታውቋል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ፤ በምግብ ሸቀጦቹ ላይ የተጣለው ቀረጥ በመነሳቱ በተለይ በምግብ ዘይት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ እየታየ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ይህን ተከትሎ ከ3 ወራት በፊት 480 ብር ይሸጥ የነበረው 5 ሊትር የሱፍ ዘይት፣ አሁን ላይ ከ280 እስከ 320 ብር እየተሸጠ ነው ያሉት ሓላፊው፤ ምርቶቹን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት የሚችሉትም የራሳቸው የውጪ ምንዛሬና የባንክ ፍቃድ ያላቸው አስመጪዎች ፣ እንዲሁም የምግብ ሸቀጦች አስመጪነት ፍቃድ ያላቸው መሆናቸውም ታውቋል።
እንደሚኒስቴር መ/ቤቱ መግለጫ ከሆነ እስካሁን 10 የተፈቀደ የዲያስፖራ አካውንት ያላቸው አስመጪዎች ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፤ ለመጪው የአዲስ ዓመት በዓልም አሁን በአስመጪዎች ከቀረጥ ነፃ ከገቡት የምግብ ዘይቶች በተጨማሪ በመንግሥት 56 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ኦይል የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ መግባታቸው ተረጋግጧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሕብረተሰቡ የበዓል ሸመታውን ተረጋግቶ እንዲያሳልፍ ታስቦ ለበዓሉ የስኳር እጥረት እንዳይከሰት 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ተገዝቶ ወደ ሀገር ቤት እየገባ ነው መባሉንም ሰምተናል።
ለሰዎች መሠረታዊ የእለት ፍጆታ የሆነው ስኳር በሀገር ውስጥ እየተመረተ የሚሰራጭ ቢሆንም፤ ፍላጎት ከአቅርቦት በላይ በሚሆንበት ጊዜ ከውጭ ተገዝቶ እንዲሸፈን የሚደረግ መሆኑ ታውቋል። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ጨምሮ ለመጪው 2 ወራት ለፍጆታ የሚሆን በቂ የስኳር ክምችት ስላለ እጥረት አይከሰትምም ተብሏል።
ነገር ግን ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ምርት በመሸሸግ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር ስለሚያደርጉ የቁጥጥር ስራውን ጠበቅ አደርጋለሁ ሲል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡