ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በጋምቤላ ክልል እስካሁን 863 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው የሠባት ሰዎች ሕይወት ከማለፉ ባሻገር የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ቢስፋፋም ክልሉ ዕለታዊ ሪፖርቶችን ማቆሙ ታውቋል።
ከሳምንታት ወዲህ ክልሉ እንደ ሌሎች ክልሎች የኮቪድ- 19 ዕለታዊ ሪፖርቶችን በመደበኛነት ማቆሙን የክልሉ ጤና ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ወንድምአገኘሁ በላይነህም አረጋግጠዋል።
“የናሙና ምርመራ ውጤት ቀጥታ ለኮሚዩኒኬሽን ክፍል አይላክም። የኢመርጀንሲ ኦፕሬሽን ሴንተር ከተላከ በኋላ ነው ወደ ኮሚዩኒኬሽን የሚልኩት። በየቀኑ መረጃ መውጣት እንዳለበት ተማምነናል። በየቀኑ አለመውጣቱ ሰውን ያዘናጋል” ያሉት ሓላፊው ከሕዝብ እየቀረበ ያለውን ቅሬታና ክፍተቱን ለመሸፈን እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በየቀኑ ውጤት እየወጣ አይሁን እንጂ ምርመራ ግን አልተቋረጠም ያሉት ባለሙያው የክልሉን ነዋሪ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራም እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።