ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ሕክምና በሚሰጥባቸው ሆስፒታሎችና በለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች ከክፍያ ጋር በተያያዘ በመንግሥት የተገባላቸው ቃል እንዳልተፈጸመ ተናገሩ።
እነዚህ የኮቪድ 19 ሕክምና በሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎችና አጋዥ ሠራተኞች ይሰጣችኋል የተባሉት የአበል ክፍያ ተፈፃሚ ባለመደረጉ ፣ ያቀረቡትም ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ቅሬታቸው ተጠናክሮ መቀጠሉን ሠራተኞቹ በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ላይ ከሰጡት አስተያየት መረዳት ተችሏል።
በጳውሎስ ሆስፒታል የኮቪድ 19 ሕክምና በሚሰጠው ሕንፃ ላይ በፅዳት ሠራተኝነት የተቀጠሩ ግለሰቦች ለተከታታይ 3 ወራት ገንዘብ ማግኘት ስላልቻልን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነን ሲሉም ተደምጠዋል።
በየካቲት 12 አጠቃላይ ሆስፒታል፣ በቃሊቲ ለይቶ ማቆያና በኤካ ኮተቤ የለይቶ ማቆያ ማዕከሎች ውስጥ የሚሠሩ የፅዳት ሠራተኞችም በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት በኩል የተገባላቸውን ጥቅማ ጥቅም ያካተተው የገንዘብ ክፍያ ከተፈጸመላቸው ወራት መቆጠሩን ተናግረዋል።
ከፅዳት ሠራተኞች ባሻገር የአምቡላንስ ሹፌሮች፣ ነርሶች እና ድጋፍ ሰጪ የጤና ባለሙያዎችም በተመሳሳይ አበልን ጨምሮ ክፍያው እንዳልተፈጸመላቸው አስታውቀዋል። ሠራተኞቹ በዚህ ፈታኝ ወቅት ሙያዊና ወገናዊ ግዴታችንን ለመወጣት ራሳችንን ለአደጋ አጋልጠን ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ይህን ያህል ጊዜ ክፍያችን መዘግየቱ አግባብ አይደለም ብለዋል።
ከኮሮና ጋር በተያያዘ ከሀገር ውስጥና ከውጭ መንግሥታት እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ከፍተኛ ገንዘብ ያከማቸው የጤና ሚኒስቴር ችግሩ መኖሩን አምኖ ከአሠራር ክፍተትና ከበጀት መዝጊያ ጋር በተያያዘ ክፍያው መዘግየቱን አምኖ በጥቂት ቀናት ውስጥ አስፈላጊውን ክፍያ እፈጽማለሁ ሲል ምላሽ ሰጥቷል።