ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሥርጭት ላይ የሚገኘው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሙዚቃ ባለሙያዎች ኑሮ ላይ ችግር ማስከተሉን የሙዚቃ ዘርፍ ባለሙያዎች ማኅበር አስታወቀ።
ወደ ሀገራችን ከገባ ስድስት ወራት ሊደፍን የተቃረበው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሙዚቃ ባለሙያዎች ኑሮ ላይ ጫናው በእጅጉ መበርታቱን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ (ዶክተር) ገልጸዋል።
የገዳዮ ኮሮና ቫይረስ መከሰት በተለይ በሆቴሎችና ምሽት ክለቦች ይዘጋጁ የነበሩ የሙዚቃ መድረኮች ያለመኖራቸው የበርካቶችን የዕለት ጉርስ እንደነፈገ ያብራሩት ፕሬዝዳንቱ፤
ማኅበሩ የተወሰኑትን አርቲስቶች ችግር በጊዜያዊነት ሊፈታ ይችላል ያለውን መላ ዘይዶ መንቀሳቀሱንም ጠቁመዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ስፖንሰር በማፈላለግ “ተመልካች አልባ” ኮንሰርት በማዘጋጀት ከ100 በላይ ሙያተኞችን ማገዝ እንደተቻለ የገለጹት አንጋፋ ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ፤ በመንግሥት ድጋፍ ብቻ ችግሩ በዘላቂነት ሊፈታ የማይችል በመሆኑ እንደ ተዘዋዋሪ ፈንድ ድጎማ ለማግኘት የሚያስችል እቅድ መያዙንም አስረድተዋል።