ካለፈው ዘጠኝ አመት ጀምሮ በርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰው አገራቸው ሶሪያን እኤአ አቆጣጠር መስከረም 2,2015 ሁለቱ ልጆቻቸውን አላን እና የሁለት አመት ታላቅ ወንድሙ ጋሊቢን በአሮጌ ጀልባ ይዘው ወደ ግሪክ ለመሸሽ የወጠኑት ወላጅ አባት ኩርዲይ አብደላ እና እናታቸው ሪሀና የተሳፈሩባት ጀልባ የባህሩን ነውጥ መቋቋም ተስኗት ከቱርክ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ስትሰጥም ከአባት በቀር ሶስቱም የአላን ቤተሰቦች ሰጥመው ሞቱ።
ያ የዛሬ አምስት አመት አስክሬኑ በግንባሩ ከአሸዋማው የባህር ዳርቻ ላይ ተደፍቶ በባህር ጠረፍ ጠባቂዎች አማካኝነት የተገኘው ጨቅላው አላን ኩርዲይ በወቅቱ የበርካታ የአለማችን ህዝቦች ልቦችን ክፉኛ ሰብሯል፣ብዙዎችም ውስጣዊ እንባቸውን አንብተውለታል።
እኤአ ከ 2014 ጀምሮ አላንን የመሰሉ ይህቺ አለም ፊቷን ያዞረችባቸው በግምት ከሃያ ሺህ በላይ ኢትዮጵያኖች፣ ኤርትራኖች፣ሱዳኖች፣ሶሪያኖች፣ሶማሌዎች ወዘተ የተሻለ ህይወት ፍለጋ፣ ህልማቸውን እውን ሳያደርጉ ለባህር ሲሳይ ሆነዋል። በአገራቸውም እንደዚሁ መከራቸውን የሚያየትን ቤት ይቁጠራቸው።
ከጀርመን ሆነው አምስተኛው አመት ዝክረ አላንን ያከበሩት አክስቱ( የአባቱ እህት) ቲማ ኩርዲይ” በአለማችን ላይ አላንን የመሰሉ የእርስ በርስ ጦርነት እና መሰል ችግሮች ሰለባዎች ዛሬም ተበራክተዋል፣ከመቼውም ጊዜ በከፋ እገዛችንን ይሻሉ።እነዚህ ወገኖቻችንን ልንረዳቸው እንጂ፣ አይናችንን ልንጨፍንባቸው፣ጀርባችንን ልንሰጣቸው እና ልንሸሻቸው አይገባም።”ሲሉ ተማጽነዋል።አላን ዛሬ በህይወት ከአጠገባችን ቢኖር ኖሮ የባለ ስምንት አመት የሚያጓጓ ልጅ ይሆን ነበር። ነፍስ ይማር አላን፣ (rest in peace፣arqid fi salam, ارقد في سلام)።