ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– 60 ሺኅ ብር ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ በተያዘ የሥራ ሓላፊ ላይ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 3 አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ቁጥጥር ሓላፊ የሆነው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው ትናንት ነሃሴ 27 ቀን 2012 ዓ/ም ነበር።
በክ/ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ተወካይ ሓላፊ ረዳት ኢንስፔክተር እሸቱ ቅጣው ፤ ዶክተር አድል አብደላ የተባሉት የግል ተበዳይ በረንዳ ለመሥራት ፈልገው ወደ ወረዳው በመሄድ የግንባታ ፈቃድ ጠይቀው ከተፈቀደላቸው በኋላ ግንባታ ቢጀምሩም የአስተዳደሩ የቁጥጥር ሠራተኞች ወደ ግንባታው ስፍራ በመሄድ በተፈቀደው መሰረት እየተገነባ አይደለም በማለት፣ በተጀመረው መንገድ መቀጠል ካስፈለገ የግል ተበዳይ 150 ሺኅ ብር እንዲሰጡ መጠየቃቸውን አስረድተዋል።
የግል ተበዳይ ግን 150 ሺኅ ብር የለኝም በማለታቸው የጉቦ ገንዘቡ ወደ 80 ሺኅ ብር ዝቅ እንደተደረገላቸው እና ከዚያ በኋላ ሁኔታውን ለፖሊስ ማሳወቃቸውን የገለጹት ረዳት ኢንስፔክተሩ፤ 80ሺኅ ብር እንደሌላቸው በአካልም በስልክም ተገናኝተው ከተደራደሩ እና በ60 ሺኅ ብር ከተስማሙ በኋላ ተጠርጣሪው ብሩን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን አስታውቀዋል።
ጉዳዮን አስመልክቶ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ትስስር ገፆች ተጠርጣሪው የተቀበለው ገንዘብ 140 ሺህ ብር እንደሆነ ተደርጎ የተገለፀው ስህተት በመሆኑ እርምት እንዱዲወሰድበትም ኢንስፔክተሩ አሳስበዋል።