ትዴት፣ ኢዜማና ህብር ኢትዮጵያ በህወሓት ላይ ጠንካራ ውሳኔ እንዲተላለፍ ጠየቁ

ትዴት፣ ኢዜማና ህብር ኢትዮጵያ በህወሓት ላይ ጠንካራ ውሳኔ እንዲተላለፍ ጠየቁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ በሚያካሂደው አስቸኳይ ስብሰባ የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት ጠንካራ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚገባ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሳሰቡ።

የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ ህብር ኢትዮጵያና ኢዜማ ፤የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፊታችን ረቡዕ በትግራይ ክልል ለማካሄድ ከታሰበው ክልላዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በገዢው ፓርቲና በህወሓት መካከል ያለውን ውጥረት በዘለቄታዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ውሳኔ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅበት ዛሬ ለንባብ ለበቃው ለአዲስ ዘመን ገልጸዋል።
 ህወሓት ለማካሄድ ያሰበው ምርጫ ህገመንግሥቱን የጣሰ ነው ያሉት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴት) ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፤ “በተለይም መላው ዓለም በኮረና ወረርሽኝ በተናወጠበትና ምርጫ ባስተላለፈበት በዚህ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫው እንዲራዘም ያስተላለፈውን ውሳኔ የጣሰ ተግባር ፈጽሟል። ህወሓት ምርጫውን ለማካሄድ ህገ መንግሥታዊ የጊዜ ገደብ ምክንያት ቢያደርግም ዋና ዓላማው ግን ትግራይን ከሌላው ሕዝብ ለመገንጠል ያለመ ነው” ሲሉ የቀደምት ድርጅታቸውን እኩይ ተግባር አጋልጠዋል።
ይህ ምርጫ ህወሓቶች ላለፉት 27ዓመታት በመላው ሃገሪቱ ያደረሱትን ጥፋትና ጉዳት ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያደርጉት ሽሽት እንደሆነም ያመላከቱት አረጋዊ በርሄ፤  የህወሓት አመራሮች ምርጫውን የሚያካሂዱት ለእውነተኛ ዲሞክራሲ መስፈን በማሰብ ሳይሆን በተገነጠለች ትግራይ ተዝናንተው ለመኖር ያቀዱት ሴራም ነው ብለዋል።
 ምርጫው የትግራይ ህዝብን ወንድም፣ እህት ከሆነው ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያጋጩት  ያቀዱበት ስለሆነ ዜጎች እዚህ ላይ ነገሮችን በጥልቀት ማየት ይኖርባቸዋል ሲሉም የመከሩት የትዴት ሊቀመንበር “ህወሓት የሚከተለው አካሄድ አደገኛ በመሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫውን የሚያስቆም ጠንከር ያለ ውሳኔ ማስተላለፍ ይገባዋል” ሲሉም ጠይቀዋል።
 ጦርነት ማወጅም ሆነ የትግራይ ህዝብን ለሞት የሚዳርግ ማንኛውም እርምጃ ፓርቲያቸው መኖር አለበት ብሎ እንደማያምን የተናገሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፤ ይልቁንም የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን መውሰድ፣ ፋይናንስ ከመከልከል ጀምሮ የኮምዩኒኬሽንና የትራንፖርት አማራጮችን በመዝጋት ህወሃትን ከጥፋት ጎዳናው መመለስ ይገባል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ህወሓት አካሂደዋለሁ የሚለውን ምርጫ አስመልክቶ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ህዝብን ለጉዳትና ለጦርነት ከሚማግድ አማራጭ ውጭ የሆኑ ወሳኝ እርምጃዎችን በመውሰድ የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ኢዜማና ህብር ኢትዮጵያም ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY