የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ያወጣው የፕሬስ መግለጫ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ያወጣው የፕሬስ መግለጫ

ቀን፡- 30/12/2012
አዲስ አበባ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዙር የፓርላማ ዘመን 5ኛ አመት 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ወደ ጎን በመተው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 እና አዋጁን መሰረት አድርጎ ያቋቋመው የምርጫ ኮሚሽን፣ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እና የፈፃማቸው ተግባራት የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔ እንዲሰጥበት በሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ተጣርቶ ለመጨረሻ ውሳኔ ለምክር ቤቱ በሕገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኩል በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱም ላይ በእስከ አሁኑ ሂደት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ክብር ያለው መሆኑንና ህገወጥ አካላት በሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ብሎ የሚያምን መሆኑ እና በቀጣይም ምክር ቤቱ ለትግራይ ሕዝብ ካለው ውግንና አንጻር ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት እንዳይደረስ ችግሮችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በተጨማሪ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ እና የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በመጥቀስ የትግራይ ክልል እያካሄደ ካለው ህገወጥ ምርጫ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብት አለማክበር ተቀባይነት የሌለውና ሊታረም የሚገባው መሆኑ ምክር ቤቱ አስቀምጠዋል፡፡

በሌላ በኩል የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ እና የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ በደብዳቤ ሕገ መንግስቱና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር የሰጡትን ማሳሰቢያ አለመቀበሉ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው መሆኑን ምክር ቤቱ መግባባት ላይ ደርሷል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሚከተሉትን የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች በሙሉ አፅድቋል፡፡

1) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 55(15) እና አንቀጽ 55(2)(መ) ጋር ይቃረናል፤

2) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012ን መሰረት አድርጎ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ስልጣን ይጥሳል፤

3) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት፣ አስፈፃሚ አካላት እና የምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 ያሳለፏቸው ውሳኔዎች እና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የመጨረሻ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

LEAVE A REPLY