የሃይማኖት አባቶች ከውሸት ይቅርታ በመራቅ በእውነት ብቻ መመላለስ ይገባል ሲሉ ተናገሩ

የሃይማኖት አባቶች ከውሸት ይቅርታ በመራቅ በእውነት ብቻ መመላለስ ይገባል ሲሉ ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ፤ የይቅርታን ትልቅነት በማስገንዘብ አዲሱን ዓመት በእውነተኛ ይቅርታ እንሻገር የሚል መልእክት አስተላለፉ።

”በዓለማችን ታሪክ ውስጥ የሰዎችን ግንኙነት አስተማማኝና ሰላማዊ ጠንካራና ተስፋ ያለው እንዲሆን ከሚያደርጉት መሰረታዊ የህይወት ክንውኖች ዋናው ይቅርታ ነው” ያሉት ፓትርያርኩ፤ “በአሮጌው ዘመን ባደረግነው በደል ሁሉ ፈጣሪ ይቅር እንዲለን በየእምነታችን ይቅርታን መጠየቅ ይገባል” ም ሲሉ ተናግረዋል።
መጪው ዘመን የሰላም፣ የአንድነት እና የስምምነት ዓመት እንዲሆን የተመኙት ብፁዕነታቸው፤ በሃገር ውስጥና በውጭ ላሉ ኢትዮጵያዊያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ  ዑመር እድሪስ በአሮጌው ዘመን የተሠሩትን ሃጥያቶች ባለመድገም በይቅርታ ወደ አዲሱ ዘመን መሻገር ይገባል ነው ያሉት።
ይቅርታው አንደበታዊ እና አፋዊ ሳይሆን ልባዊ ይቅርታ መሆን እንዳለበት አበክረው ያሳሰቡት ተቀዳሚ ሙፍቲ፤ በደል ፈጻሚ ወደ ጥፋቱ ዳግመኛ ላይመለስ የይቅርታን በጎነት ሊተገብረው እንደሚገባም ምክር ለግሰዋል።
በሃገር ሰላም የሚሰፍነውና ወደ እድገት መሄድ የሚቻለው በልባዊ ይቅርታ መጓዝ ሲቻል መሆኑን የጠቆሙት የሃይማኖት አባት “ከውሸት ይቅርታ በመራቅ በእውነት ብቻ መመላለስ ይገባል” ሲሉ ይቅርታው ከፖለቲካ ትርፍ እንዲዘል ጠይቀዋል።
ሊቃነጳጳስ ዘካቶሊካዊያን ብጹህ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶም በተመሳሳይ  ”ከሁሉ በላይ የበደልነው አምላካችንን ነውና ይቅር በለን ብለን ዘመኑን ልንሻገር ይገባል” የሚል መልእክት ለኢትዮጵያውያን አስተላልፈዋል።

LEAVE A REPLY