ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዛሬ የዋለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በእነ ጃዋር የቅድመ ምርመራ መዝገብ ላይ የቀረበውን የዋስትና መብት ውድቅ አደረገው።
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ዐቃቤ ሕግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን አሰምቶ በመጨረሱ ፍርድ ቤቱ ክስ የሚመስርትበትን ጊዜ ለመስጠትና ተጠርጣሪዎች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ትዕዛዝና ውሳኔ ለማስተላለፍ ለዛሬ ቀጠሮ መያዙ አይዘነጋም።
ዐቃቤ ሕግ ክስ ለመመስረት፣ የቅድመ ምርመራ ግልባጭ ከደረሰው በኋላ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንደሚመሰርት ፍርድ ቤቱ አርብ እለት ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር፤ ጠበቆች በበኩላቸው የቅድመ ምርመራ ከተጠናቀቀበበት ቀን ጀምሮ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ክስ ይመስርት ሲሉ ክርክር አድርገዋል፤ በሰዐቱ።
ፍርድ ቤቱ ይህን ክርክር ተከትሎ ዛሬ ባሳለፈው ውሳኔ ዐቃቤ ሕግ ከ1 እስከ 10 ተራ ቁጥር በሚገኙ ተጥረጣሪዎች ማለትም በአቶ ጀዋር መሐመድ፣ በአቶ በቀለ ገርባ፣ በአቶ ያለምወርቅ አሰፋ፣ በአቶ ጌቱ ተረፈ፣
በአቶ ታምራት ሁሴን፣ በአቶ በሽር ሁሴን፣ በአቶ ሰቦቃ ኦልቀባ፣ በአቶ ኬኔ ዱሜቻ፣ በአቶ ዳውድ አብደታ እና በአቶ ቦጋለ ድሪሳ ላይ እስከ መስከረም 8/ 2013 ዓ.ም ድረስ ክስ ይመሥረት ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የቅድመ ምርመራ ግልባጭም ለዐቃቤ ሕግና ጠበቆች ከጳጉሜን 2/2012 እስከ ጳጉሜን 5/2012 ዓ.ም ድረስ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ አዝዟል።
በተያያዘ ዜና በእነ አቶ ጃዋር ቅድመ ምርመራ መዝገብ ከ11-14 ባሉት ተጠርጣሪዎች፤ በአቶ ሐምዛ አዳነ፣ በአቶ ሸምሰዲን ጣሃ፣ በአቶ ቦና ቲብሌና በአቶ መለሰ ድሪብሳ ላይ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ አቅርቦ ስላላሰማ ክስ የሚኖረው ከሆነ በአምስት ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ጃዋር መሐመድና በቀለ ገርባን ጨምሮ በመዝገቡ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች፤ በነሐሴ 29/2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ችሎቱን ጠይቀው መጠየቃቸውን ተከትሎ ጉዳዮን የመረመረው ችሎቱ የእነ ጃዋርን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል።