ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከነገ ወዲያ (ረቡዕ) ጳጉሜ 4/2012 ዓ.ም ይካሄዳል የተባለውን የትግራይ ክልል ምርጫን ለመዘገብ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ዛሬ ረፋድ በመጓዝ ላይ የነበሩ የሃገር ውስጥና የውጪ ጋዜጠኞች ከቦሌ የአውሮፕላን ማረፊያ እንዳይሄዱ ተከለከሉ።
ብዙ ሲያወዛግብ የቆየው የትግራይ ክልል ምርጫን አስመልክቶ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ በካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው ምርጫው ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ ሕገ ወጥ ነው ሲል በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም።
ህወሓትና ብልፅግናን ክፉኛ ካቃቃረው ምርጫ ጋር ለተያያዘ ሥራ በአውሮፕላን ሊጓዙ የነበሩት ጋዜጠኞች ቁጥራቸው ከ10 በላይ እንደሆነም ታውቋል።
ጋዜጠኞቹ በበረራ መርሃ ግብራቸው መሰረት ወደ አውሮፕላን ከገቡ በኋላ ነው ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ የተደረገው።
“የተወሰንን ሰዎችን መታወቂያ ካርድ ከተመለከቱ በኋላ ተሳፍረንበት ከነበረው አውሮፕላን ተገደን እንድንወርድ ተደርገናል” ያለው መቀሌ ተጓዥ ከነበሩት ጋዜጠኞች መሀል አንዱ የሆነው ለብሉምበርግና ለቪኦኤ (አሜሪካ ድምፅ) የሚሠራው ሳይመን ማርክስ ነው።
ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ መቀለ ሊጓዝ በነበረው አውሮፕላን ውስጥ ሠላሣ የሚደርሱ መንገደኞች የነበሩ ሲሆን፣ የአውሮፕላን ማረፊያው የደኅንነት ሠራተኞች የተሳፋሪዎቹን መታወቂያ ከተመለከቱ በኋላ ተጓዦቹ እንዲወርዱ ስማቸውን ያልጠቀሱ ተሳፋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፀጥታ ሠራተኞቹ የመንገደኞቹን ሞባይል እና ላፕቶፕ ሲቀበሉ መመልከታቸውን የጠቆሙ ሌላ መንገደኛ ደግሞ በረራውም ሳይሰረዝ እንዳልቀረ አስረድተዋል።
ወደ መቀለ እንዳይጓዙ ከተደረጉ ተሳፋሪዎች መካከል የዓለም ዐቀፉ የቀውስ ጉዳዮች አጥኚ ተቋም የኢትዮጵያ ተመራማሪ የሆነው ዊሊያም ዳቪሰንም ይገኝበታል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል ሮይተርስ ወደ መቀሌ ለማምራት በዝግጅት ላይ የነበረው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ መንገደኞችን ዋቢ አድርጎ በሠራው ዘገባለ ላይ አራት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 12 የሚሆኑ ሰዎች ወደ መቀሌ በረራ ለማድረግ ከተዘጋጀው አውሮፕላን ውስጥ እንዲወርዱ ተደርጓል።