ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ቀጣዮና ስድስተኛው ዙር ሃገራዊ መርጫ ሊካሄድ እንደሚችል የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት አስታወቁ።
በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት አስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ እንዲሸጋገር የተወሰነው ምርጫ እንዲካሄድ የወረርሽኙ ሁኔታን በተመለከተ ከጤና ባለስልጣናት የሚሰጡ ምክሮችን መሰረት እንደሚያደርግ መነገሩ አይዘነጋም።
በሃገሪቱ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታን በተመለከተ የመስሪያ ቤታቸውን ግምገማ ለሕዝብ ተወካዮች ምከክር ቤት ያቀረቡት ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በያዝነው ዓመት ሃገራዊ ምርጫን ለማካሄድ ይቻላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ካለው የወረርሽኝ ስጋት አንጻር የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ የምርጫ ሥነምግባር፣ ደንብና ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን በማዘጋጀት በአንድ ዓመት የተራዘመውን ሥድሥተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል የጤና ሚኒስትሯ ይፋ አድርገዋል።
ምርጫውን ለማካሄድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ካጋጠመ፤ ይህ በተለየ ሁኔታ መታየት ሊያስፈልገው እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉም ዶክተር ሊያ ታደሰ በሪፖርታቸው ይፋ አድርገዋል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ወረርሽኙ በሁሉም ክልሎች የተሰራጨ ሲሆን፤ በዚህም የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የታወቀ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ እስካሁንም በተደረገው ምርመራ ከ66 ሺኅ 200 ሰዎች በላይ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና 1 ሺኅ 45 ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት መሞታቸውን አስረድተዋል።