ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– መስማት የተሳናቸው ዜጎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተጠቃሚ ለማድረግ መመሪያ ማዘጋጀቱን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።
በአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አዋጅ መሰረት በማድረግ መስማት የተሳናቸው ዜጎች የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ገብተው ፣ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና በመውሰድ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንዲችሉ መመሪያ ማዘጋጀቱን ተቋሙ ይፋ አድርጓል።
በግንባታ ላይ ያሉ ሰፋፊ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የአካል ጉዳተኝነትን ሊያስተካክሉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤት ያካተቱ ተሽከርካሪዎችም ለትራንስፖርት አገልግሎት እየዋሉ መሆኑ እና በምልክት ቋንቋ የአሽከርካሪዎችን ስልጠና መስጠት የሚቻል በመሆኑ መመሪያው ለመሰናዳት እንደበቃ ተነግሯል።
የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ስርዓቱ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች አመቺ በመሆኑ፣ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተጠቃሚ ማድረጉ በተሸከርካሪዎች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ዕድል የሚሰጥ ነውም ተብሎለታል።
የመመሪያው መዘጋጀት ዋና አላማም መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የአሽከርካሪ ማረጋገጫ ፈቃድ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋትና ተግባራዊ በማድረ፣ ተሸከርካሪን በማሽከርከር ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና ሰርቶ የመኖር መብታቸው እንዲከበር ማድረግ እንደሆነም ይፋ ተደርጓል።
መስማት የተሳናቸው ሰዎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለማግኘት በአዋጁ መሰረት ለየምድቦቹ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃና የማሽከርከር እድሜ ገደብ፣ የጤና ምርመራ ውጤት እና ሌሎችም አስፈላጊ ማስረጃዎችን መሟላት አለባቸው ሲል ባለሥልጣን መ/ቤቱ ይፋ አድርጓል።
የአሽከርካሪ ብቃት ስልጠና የሚሰጡ ተቋማትም መስማት ለተሳናቸው ዜጎች የሚሰጥ ስልጠናን የምልክት ቋንቋ በሚችል አሰልጣኝ ወይም አስተርጓሚ በመታገዝ መስጠት እንደሚችሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡
የተግባር ስልጠናውም በተመሳሳይ ተሽከርካሪዎች ይሰጣል ተብሏል፡፡
መስማት የተሳናቸው እጩ አሽከርካሪዎች የንድፈ ሀሳብ ፈተና በኮሚፒውተር ወስደው ወጤቱን እንዲያውቁ እና ብቻቸውን እያሽከረከሩ የተግባር ፈተና እንዲወስዱ በመመሪያው ተካቷል፡፡