ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮች በ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ቁርጠኝነት ያስፈልጋቸዋል ተባለ

ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮች በ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ቁርጠኝነት ያስፈልጋቸዋል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች የ2030 የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የጀመሩትን ቁርጠኝነት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።
አመታዊው በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ኢትዮጵያ በኢስታንቡል የድርጊት መርሃ ግብር መሠረት እያካሄደች ያለውን የልማት እንቅስቃሴና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
በመላው ዓለም የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮችን የመልማት ጥረት በእጅጉ መጉዳቱን የጠቆሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤
በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተጨማሪ ድህነት፣ ሥራ አጥነት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በልማታቸው ላይ ከፍተኛ ተግዳሮቶች ሆነውባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ተግዳሮቶች በመቋቋም የገጠር ልማትን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ብዙ ርቀት ተጉዛለች ያሉት ገዱ አንዳርጋቸው፤ ኢትዮጵያ የማኅበራዊና የቁሳዊ መሠረተ ልማቶችን በስፋት በማስፋፋት የ2030 ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳከት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰች ነው ማለታቸው ታውቋል።
በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮች የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችንና በኢንስታንቡል የድርጊት መርሃ ግብር የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ቁርጠኝነታቸውን ይበልጥ አጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸውም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳስበዋል።
በልማት ወደኋላ የቀሩ አገሮች ቡድን ስብሰባ ላይ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ የ47 አገራት ሚኒስትሮች፣ አጋር አገሮች እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይና ሌሎች ተጋባዦች ተሳትፈዋል።

LEAVE A REPLY