የኢትዮጵያ መንግስት የመሀል አገር መንግስት ነው፤አራሹ፤ ቆፋሪው፤ ወርቅ አጥላዩ በዳር አገር የሚኖረው ህዝብ ሆኖ ሳለ እንደ ዜጋ እሚቆጥረው የለም፤ መብራት ባታስገባለት ክሊኒክ ባትከፍትለት የረባ ፖሊስ እን ኳን አትመድብለትም? ባንድ ከተማ ውስጥ ብዙ ሰው ባንዴ ሲሞት መከላከያ ሰራዊት የት ነበር? በመዲናይቱ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ ሁለተኛውን ዙር የሰልፍ ትርኢት ለማሳየት እያሟሟቀ ይሆናል !
መንግስት ሰላማዊ ሰው ጦር መሳርያ እንዲታጠቅ አይፈልግም ! ያም ሆኖ ትጥቅ ካስፈታ ሁሉንም መሆን አለበት ፤ ትጥቅ ማለት ክላሽና ሽጉጥ ብቻ አይደለም! ባገር አማን ቀስትና ደጋን ተሸክሞ መወዛወዝ መከልከል አለበት! በዳር አገር የሚኖሩ ሽፍቶች የሚታጠቁት ቀስት ጫፉ መርዝ አለው! መንግስት ደንበኛውን ጦር መሳርያ ከልክሎ የኬሚካል ጦር መሳርያ የሚፈቀድበት ምክንያት አይገባኝም! እዚህ አገር ደጋን መፈቀድ ያለበት ለፈታይ ብቻ ነው!
ክልሎች በየጊዜው እያስመረቀኑ የሚያስወጡት “ልዩ ፖሊስ” ስፍር ቁጥር የለውም! እንዲያውም የዘመናችን ወጣት በሁለት ሊከፈል ይችላል! የዩንቨርሲቲ ተማሪና ልዩ ሃይል ተብሎ! አብዛኛው የክልል ልዩ ሃይል ግጭት ሲነሳ ግጭቱን ለማብረድ ይለግማል! ጭራሽ የእብድ ገላጋይ ሆኖ ዱላ ያቀብላል!
ልዩ ሃይሎች የሰለጠኑ ናቸው! ስልጠናው ግን የእሳት ቀለበት መዝለል፤ ጣውላ ጀርባ ላይ መስበር፤ ተጋጣሚን በጅዶ ማነጠፍ ወዘተ ..ነው:: የአእምሮና የመንፈስ ስልጠና ይሰጣቸዋል!? አይመስለኝም! ፖሊሶች ዜጎችን ዘር ሃይማኖት እና ሃብት ሳያበላልጡ ማገልገል እንዲችሉ ሁነው መሰልጠን አለባቸው!
ባጠቃላይ ባገራችን የሰላም አስከባሪ ሃይል እሚባለው ፋይዳው አጠራጣሪ ነው፤ የቀድሞ ዘበኛችንን ያስታውሰኛል!
ከሁለት አመት በፊት የረር በር ውስጥ ስኖር ሌባ እያስቸገረኝ አንድ ሽማግሌ ዘበኛ ቀጥሬ ነበር! ዘቡሌው የተቀጠሩ ቀን አጥሩን ሽቅብ ገመገሙትና “ግንቡ አጭር ስለሆነ ነው ያጋለጠህ! ትንሽ ወደላይ ይርዘም “ የሚል ሀሳብ አቀረቡ! ከዚያ ግንበኛ ልጃቸው አምጥተውልኝ ከፍየው፤ ግንቡ ወደላይ ለጠጠው! ያ በሆነ በሶስተኛው ቀን ግቢያችን ውስጥ ሌባ ገባ!
ቤት ውስጥ ሆኘ ደውየ ቀሰቀስኳቸው፤
‘’ ሌባ ገብቷል ይነሱ ” አልኳቸው
“ እንዴ? በየት በኩል” አሉኝ
“ በግንቡ ዘሎ ዱብ ሲል በመስኮት አይቻለሁ”
በፉከራ ግቢውን ይቀውጡታል ብየ ስጠብቅ ፤ እንዲህ አሉኝ፤
“ተርፏል ግን ! “?