የዜጎችን የመኖር መብት ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ስለ ብልፅግና ማውራት እንደማይችል ኢዜማ አሳሰበ

የዜጎችን የመኖር መብት ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ስለ ብልፅግና ማውራት እንደማይችል ኢዜማ አሳሰበ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማክበር እና ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልፅግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም ሲል ኢዜማ አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባላት እና አመራር በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በግፍ በተገደሉ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይፋ ባደረገበት መግለጫው ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል።
በክልሉ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደረሰው ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ እና በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ችግር ፈቺ ያልሆኑ ምላሾች፣ የችግሩ ምንጭ አካባቢውን ከሚያስተዳድረው የመንግሥት መዋቅር እና ችግሩን በቸልታ እያየ ያለው የፌደራል መንግሥት ነው ብለን እንድናምን አስገድዶናል ያለው በፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ፓርቲ፤ ከዚህ በፊት የተፈፀሙ ጥቃቶች አጥፊዎች እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮች ላይ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ባለመወሰዱ ችግሩ አሁንም እንዲቀጥል እድል ሰጥቷል ሲል ገልጿል።
ክልሉን በሚመሩት ኃላፊዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ካልተወሰደ ግድያና ማፈናቀሉ ይቆማል ብሎ እንደማያምን የጠቆመው ኢዜማ፤ የፌደራል መንግሥት እንደዚህ ዓይነቱ ጥቃቶች ከመድረሳቸው በፊት የመከላከል እና በቶሎ የማስቆም ሥራ ከምንም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው  የሚገባ ጉዳይ ነው ሲል አስጠንቅቋል።
የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን በሕይወት መኖር ማክበር እና ማስከበር እንደሆነ የጠቆመው ኢዜማ፤ ይሄን ማድረግ ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልፅግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም ብሏል።

LEAVE A REPLY