69 ሚሊዮን ዶላር ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ ለግለሰቦችና ድርጅቶች ንግድ ባንክ መስጠቱ...

69 ሚሊዮን ዶላር ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ ለግለሰቦችና ድርጅቶች ንግድ ባንክ መስጠቱ ተጋለጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት የሃገሪቱ ባንክ ባዶ እንደሆነ ቢገልጹም ንግድ ባንክ በለውጡ ማግስት፤ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከብሔራዊ ባንክ ደንብ እና መመሪያ ውጭ ሲባክን መቆየቱ ተሰማ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአቶ በቃሉ ዘለቀ ይመራ በነበረበት በ2010 ዓመት ከግንቦት እስከ ነሀሴ ከባንኩ በትንሹ ከ69 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ (የውጭ ምንዛሪ ) ከመመሪያ ውጪ ለተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እንደተሰጡ የሚያሳይ ሰነድ መገኘቱን ሸገር ራዲዮ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጪ  ሀገር ገንዘብ ወይም የውጪ ምንዛሪ ድልድልን አስመልክቶ ያወጣው መመሪያ ቁጥር FXD/51/2017፣ ለኮንስትራክሽን ድርጅቶች  የግንባታ ማሽኖች መለዋወጫ ለማስገባት ለአንድ የግዢ ማቅረቢያ ከ50,000 የማይበልጥ የአሜሪካ ዶላር እንዲመደብ ቢፈቅድም፤ መመሪው ከወጣ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት የአሠራር ጥሰት ተፈጽሟል።
በተለይም በ1ኛው ወቅት በቁጥር 36 ለሚሆኑ፣ በሌላኛው ወቅት ደግሞ 46 ለሚሆኑ የውጭ  ምንዛሪ ጠያቂዎች ለእያንዳንዳቸው ከመመሪያው ውጪ ከ50 ሺኅ የአሜሪካ ዶላር በላይ ተመድቦላቸው ወይም ተሰጥቷቸው እንደነበር  መረጃው ይፋ አድርጓል።
ከራሱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወጣው እና በባንኩ የቀድሞ ፕሬዘዳንት አቶ ባጫ ጊና የተፈረመበት ይኸው ሰነድ እንደሚያሳየው ከሆነ፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በመጋቢት 2018፤ 36 ለሚሆኑ የውጪ ምንዛሪ ጠያቂዎች ለእያንዳንዳቸው ከመመሪያ ውጪ ከ50 ሺኅ ዶላር በላይ በድምሩ 19 ሚሊዮን 886 ሺኅ 137 የአሜሪካ ዶላር ፣ በነሐሴ ወር 2018 ደግሞ ለ 46 የውጪ ምንዛሪ ጠያቂዎች በድምሩ 27 ሚሊዮን 648 ሺኅ 788 የአሜሪካ ዶላር ተመድቦላቸው ነበር።
በተጠቀሰው ዓመት በግንቦት ወር 2018 መመሪያው የውጪ ምንዛሪ እንዳያገኙ ከፈቀደላቸው የሥራ ዘርፍ ውጪ ላሉ፣ ወይም መመሪያው ለማይመለከታቸው ቢያንስ 5 ድርጅቶች በድምሩ 11 ሚሊዮን 847 ሺኅ 583 የአሜሪካ ዶላር እንደተሰጠም ታውቋል።
ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ለመለስ ፋውንዴሽን 100 ሺ ዶላር፣  ለኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ 66 ሺህ 750 ዶላር ፣ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ሴንተር 500 ሺ  የአሜሪካ ዶላር ፣ ለኢዮሃ ፕሪንተር 27 ሺኅ ዶላር፣ ለብርሃኔ ወልዱ 140 ሺኅ 800 ዶላር ተሰጥቷል።
በተጨማሪ በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ለዐሥር መኪና ሻጭ ድርጅቶች ከብሔራዊ ባንክ ድልድል ውጪ 10 ሚሊዮን ዶላር ንግድ ባንኩ ሰጥቷል።

LEAVE A REPLY