ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በተጠናቀቀው ዓመት የክረምት ወራት ውስጥ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የጣና ሐይቅ ከመጠን በላይ በመሙላቱ በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ የመኖሪያ አካባቢዎችን ጨምሮ ሠፊ ቦታ በዉሃ መጥለቅለቁ ተሰማ።
የጣና ሐይቅ በየዓመቱ የክረምት ወራት ወቅት ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ የሚሞላ ቢሆንም ፣ የዘንድሮው ግን መጠኑ በጣም ከፍተኛ እንደሆነና ምናልባትም ከ30 ዓመት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከመጠን በላይ ሙሌት ማሳየቱንና ሠፊ ቦታን ማጥለቅለቁን ነዋሪዎች በመናገር ላይ ናቸው።
ጣና ሐይቅን ተጎራብቶ በሚገኘው በፎገራ ወራዳ ናበጋ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ቀሲስ ሙልዬ የጣና ሐይቅ ውሃ ሞልቶ ካፈናቀላቸው አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው። የሐይቁ ውሃ መስኩን አልፎ ቤታቸውን በማጥለቅለቁ ስድስት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ሕይወት ለመታደግ መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ መገደዳቸውን ገልጸዋል።
በአደጋው መደናገጥ በቤት ውስጥ ከነበራቸው ንብረት መካከል ለዕለት ምግብ የሚሆንና እንስሳትን ብቻ ይዘው ራቅ ብለው ወደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ተጠግተው እየኖሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በጣና ሐይቅ የውሃ ሙላት ከተጥለቀለቁት አካባቢዎች አንዱ በሆነው በፎገራ ወረዳ ዋገጠራ ቀበሌ የሚኖሩት ዲያቆን ድምጸ በዚሁ የውሃ ሙሌት የተነሳ ሥራቸውና ሕይወታቸው ከችግር ላይ መውደቁን ተናግረዋል።
ኑሯቸውን በንግድ የሚመሩና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን ለአካባቢው ነዋሪ በማቅረብ የችርቻሮ ንግድ የሚያካሂዱት እኚህ ግለሰብ ፤ ጎን ለጎን ደግሞ የእርሻ መሬት ተከራይተው ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት የግብርና ሥራን ያከናውኑ ነበር።
ሆኖም ዕቅዳቸው ግቡን ሳይመታ የጣና ሐይቅ ሞልቶ በዙሪያው ያሉ አካባቢዎችን በከፍተኛ መጠን በማጥለቅለቁ ብዙ ብርና ጉልበታቸውን ያፈሰሱበት የእርሻ መሬት በውሃው መባከኑን፣ ሩዝ የተከሉበት ማሳ ከሐይቁ በመጣው የእምቦጭ አረም መሸፈኑን ከነዋሪው ገለጻ መረዳት ተችሏል።