ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በዚህ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሀምዛ አድነን ጨምሮ ሌሎች ከሃገር ውጪ በሚገኙ 24 ሰዎች ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ዛሬ ክስ መሠረተ።
በነጃዋር ላይ ትናንት የክስ መዝገብ ይከፈትባቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ክስ ሳይመሰርትባቸው ቢያድርም፤ ዛሬ ከፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው ከሆነ፤ ሌሎች ሰዎችን ጨምሮ በእነ ጃዋርና በቀለ ገርባ ላይ ክስ ተመሥርቷል።
ከጃዋር መሐመድ፣ ከአቶ በቀለ ገርባና ከአቶ ሀምዛ አድናን በተጨማሪ ፤ የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ሓላፊ አቶ ደጀኔ ጉተማ፣ ከወራት በፊት በአሜሪካ በሚገኝ የኢትዮጵያ ቆንስላ ዲፕሎማት የነበሩት ብርሃነመስቀል አበበ ፣ ነዋሪነታቸው አውስትራሊያ የሆነው አቶ ፀጋዬ አራራሳን (በሌሉበት) ጨምሮ በአጠቃላይ 24 ሰዎች ላይ ዛሬ ክስ ተመሥርቷል።
ከተጠቀሱት ግለሰቦች በተጨማሪ ከወራት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው ቢሮው የተዘጋው የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ የሚባለው፣ ጃዋርና ግብረአበሮቹ ለጽንፈኛ ብሔርተኝነት ፖለቲካቸው የሚጠቀሙበት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይም ክስ መመሥረቱን ለማወቅ ችለናል።
ክሱ የተመሠረተባቸው ተቋምና ግለሰቦች እንደየተሳትፏቸው ፤በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ “ብሔርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ፣ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድግ” የሚሉ ክሶች እንደቀረበባቸው ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ከዚህ ሌላ ተከሳሾቹ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀልም ክስ ቀርቦባቸዋል።
መስከረም 6/2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215፤ በአጠቃላይ ዐሥር ተደራራቢ ክሶች ማስከፈቱን የጠቆመው ዐቃቤ ሕግ፤ ተከሳሾቹም ሰኞ መስከረም 11/2013 ዓ.ም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የተመሠረተባቸው ክስ ዝርዝር እንደሚደርሳቸው ከወዲሁ አስታውቋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ ትናንት ክስ የሚመሰርትበት ቀን የመጨረሻ ቀን እንደነበረና በዚሁ መሠረትም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ይመሰረታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።