ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጃዋር መሐመድን በአባልነት የተቀበለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና ፤ መንግሥት ፍላጎቱን እንደ ልቡ የመቀያየር መብት አለኝ በሚል ስሜት አሁን ላይ ምርጫ ለማካሄድ ያለውን ከፍተኛ ስሜት እያንጸባረቀ ነው ብለዋል።
“ብሔራዊ መግባባት ላይ ሳይደረስ ምርጫው እንዴት ሊካሄድ ይችላል? ምንስ ጠቀሜታ ይዞ ይመጣል?” የሚል ጥያቄ እሳቤ ቀደም ሲል ጥያቄ እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ ምርጫው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሊዘገይ መቻሉን አስታውሰዋል።
ቀደም ሲል ምርጫው እንዲራዘም የተደረገው የጤና ሚኒስቴር በሽታው አሳሳቢ መሆኑን በመግለጹ መሆኑን ያስታወሱት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ፤ አሁን ላይ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል መባሉን በበጎ እንደሚመለከቱት ጠቁመው፤ ምርጫው የተሻለ እንዲሆን ከተፈለገ ያለአግባብ የታሠሩ ፖለቲከኞች ከእስር ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።
ምርጫ መካሄድ ይቻላል መባሉ ገና በመንግሥትና በተወካዮች ምክር ቤት አለመፅደቁን ያስታወሱት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴት) ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ የጤና ሚኒስቴር ይህን ካለ ማንም ሰው ከባለሙያዎች ጥናትና ዕውቀት በበለጠ ሁኔታዎችን መገምገም ስለማይችል የእነርሱን ግምገማ መቀበል ይገባልም ብለዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ይህን ይበሉ እንጂ ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምርጫ ይካሄዳል መባሉን ጥያቄ ውስጥ እንደከተቱም በተለያየ መንገድ ገልጸዋል።
አገሪቷ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሕዝቡ የሚቀበለው ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የግድ ነው የሚሉት አረጋዊ በርሄ፤ በርካታ ግጭቶች እየተከሰቱ ባለበት ወቅት የሰላምና የመረጋጋት ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ጠቁመው፣ ከዚህም በተጨማሪ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ሁሉም ተቋሞች ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ከመገናኛ ብዙኃን አንጻር ምርጫውን ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩልነት መዘገብ ይችላሉ ወይ? የሚለውን ጨምሮ እነዚህና መሰል ጥያቄዎች በቂ መልስ እየታየባቸው ስላልሆነ፣ አጥጋቢ ውጤት እስከሚያገኙ ድረስ ምርጫው መቆየት አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል።