ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ እና የ1987 ዓ.ም ምርጫ || መሐመድ አሊ መሐመድ

ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ እና የ1987 ዓ.ም ምርጫ || መሐመድ አሊ መሐመድ

ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ እና የ1987 ዓ.ም 
ምርጫ ትዝታዬና ተያያዥ ጉዳዮች

በአፋር ኬልል፣ አይሣኢታ ወረዳ፣ ሂናሌ በምትባል ቀበሌ በ1942 ዓ.ም የተወለዱት ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ በአዲስ አበባ አተማ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ሰማን። አላህ ጀነተል ፊርዶስን ይወፍቃቸው፤ ለቤተሰብ – ዘመዶቻቸውም አላህ ሰብር ይስጣቸው!!

በግሌ ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህን የማስታውሳቸው በተለይ ከ1987 ዓ.ም ምርጫ ጋር በተያያዘ ነው። እኔ ከዚያ ቀደም ብሎ የወ/ሮ ስኅን ት/ቤት የተማሪዎች ካውንስል ፕሬዝዴንት በነበርኩበት ጊዜ ከህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ወደጅቡቲ ተሰድጄ፣ ከዚያም ተመልሼ በእስር ላይ ከቆየሁ በኋላ ስፈታ ወደ አፋር ክልል ሂጄ ነበር። ወደ አፋር ክልል የሄድኩበት ምክንያት በልጅነቴ አይሣኢታ መሐመድ ሀንፈሬ (የቀድሞው አፄ ገ/መስቀል) ት/ቤት ስለተማርኩና የአፋር ህዝብ ስላሳደገኝ ነው ማለት እችላለሁ። እኔ እዚያ ማደግ ብቻ ሳይሆን አፋርኛ አቀላጥፌ እናገር ስለነበር ከብዙ አፋር ወንድሞች ጋር የጠበቀ ቤተሰባዊ ግንኙነት ነበረኝ።

በወቅቱ በደረሰብኝ ብዙ መከራና ስቃይ ሳቢያ በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ክፉኛ ተጎሳቁዬ ነበር። በአካል ከመዛሌም በላይ ጤንነትም ሆነ ውስጣዊ ሠላም አልነበረኝም። የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ባደረሰብኝ እንግልትና ስቃይ የእኔ ስሜት የተጎዳ ቢሆንም፣ ደሴ ስማር ከትምህርቴ በተጓዳኝ በሥነ-ጽሁፍና፣ በተለይም በቲያትር ጥበብ (በአማተር ደረጃ) ሳደርግ የነበረው እንቅስቃሴ እስከ አፋር ክልል ድረስ ዘልቆ ይታወቅ ነበር። ይህም ከታዋቂው የአፋር ከያኒ – አሎ ያዮ በሩሌና ሌላው ተጠባቢ አስ-መሐመድ አልጋኔና ሌሎችም ጋር ለመቀራረብ ዕድል ፈጥሮልኝ ነበር። እነአሎ ጋር ስለኪነ-ጥበብና ተጓዳኝ ጉዳዮች ሌሊቱን ሙሉ ስናወራ እናነጋ ነበር።

የህወሓት/ኢህአዴግ የፀጥታ ሰዎች እንደሚከታተሉኝ ጠንቅቀው የሚያውቁት እነዚህ የቁርጥ ቀን ወዳጆቼ “እዚህ መጥቶ ማንም አይነካህም” በማለት ከማበረታታት ባለፈ፣ እጅግ በሚበዛ ፍቅርና እንክብካቤ የተጎዳውን መንፈሴን ለማከም ይጥሩ ነበር። ይህም አልበቃ ብሎ ከነበረኝ የኪነ-ጥበብ ፍቅርና ያለፈ እንቅስቃሴዬ (background) በመነሳት የክልሉን ባለሥልጣናት አሳምነው፣ በወቅቱ በነበረው የባህልና ስፖርት ቢሮ ሥር “የኪነ-ጥበባትና ሙያ ማሻሻያ ክፍል ኃላፊ” ሆኘ እንድመደብ አድርገው ነበር። የእነዚህንና የሌሎች የአፋር ወንድሞችን ውለታ መክፈል ሳይሆን ዘርዝሬ ስለማልጨርሰው ዝምታን እመርጣለሁ።

ወደተነሳሁበት ፍሬ-ነገር ልመለስና፣ እኔ በባህልና ስፖርት ቢሮ በኃላፊነት ተመድቤ ስሠራ በነበረበት ሠዓት ክልሉን ሲመራ የነበረው በሱልጣን አሊሚራህና ልጆቻቸው የሚመራው የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር (ALF) ነበር። የክልሉ ፕሬዝዴንትም ሀቢብ አሊሚራህ (አላህ ይራህመው) ነበር። በወቅቱ ሀንፈሬ አሊሚራህ በሽግግር መንግሥቱ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል ነበር። በ1987 ምርጫ ዋዜማ በክልሉ ALFን ለመገዳደር የሚችል ፓርቲ ይኖራል ብሎ የሚገምት አልነበረም። በሱልጣኑና በልጆቻቸው ተፅዕኖ ሥር የነበረው ALF ደግሞ በኢትዮጵያ አንድነትና ባንድራ የማይደራደር፣ በተለይም ለባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጥና የህወሓት/ኢህአዴግን “የበዳይነትና ተበዳይነት” ከፋፋይ ትርክት የማይጋራ ነበር።

ይህ የፓርቲው አቋም፣ በግሌ “በምን ላግዛቸው እችላለሁ?” ብዬ እንዳስብ ግድ ብሎኛል። በወቅቱ የክልሉ መናገሻ በነበረችው አይሣኢታ ከተማ በተዘረጋ ገመድ (cable) አማካኝነት ለከተማው ነዋሪ የሚሠራጭ የሚኒ-ሚዲያ አገልግሎት ነበር። እኔም ያን ሚኒ-ሚዲያ በመጠቀም ALF በምርጫው እንዲያሸንፍ ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረግ ጀመርኩ። ፓርቲው እንዲያሸንፍ ከነበረኝ ብርቱ ፍላጎት አንፃር ቀንም ሆነ ሌሊት እንቅልፍ አልነበረኝም። ይህን የምሠራው በተለይ ያዮ አፍኬኤ (አላህ ይራህመውና) ጋር ነበር። ያዮ አፍኬኤ በወቅቱ በክልሉ ም/ቤት የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት የአም-አፍኬኤ ልጅ ሲሆን፣ በአጋጣሚ እኔ ባህልና ስፖርት ቢሮ ስመደብ ደብዳቤው የተፈረመው በእሳቸው ነበር።

በዚህ ሁኔታ ALF እንዲያሸንፍ ወጥረን በምንሠራበት ጊዜ አንድ አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ። ይኸውም ALF በድንገት ለሁለት ተከፈለ የሚል ነገር መሰማቱ ነበር። ለካስ ህወሓት/ኢህአዴግ በወንድማማቾቹ (ሀቢብና ሀንፈሬ) መካከል በመግባት፣ በተለይም ሀንፈሬን የሚደግፉ በመምሰል በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ብዥታ ከመፍጠራቸውም በላይ ALF ራሱን በራሱ ታግሎ እንዲጥል አደረጉት። በምርጫው ሀንፈሬ አሊሚራህን ጨምሮ ጥቂት የALF አባላት ብቻ ነበሩ መመረጥ የቻሉት። አብዛኛው የክልሉ ም /ቤት ወንበር የተያዘው ህወሓት እንዳደራጀው ሲነገር በነበረው “አዴይ” በተሰኘ ፓርቲ አባላት ነበር።

ይሁንና “አዴይ” የተሰኘው ፓርቲ በወቅቱ በህዝቡ ዘንድ የማይታወቅና የድጋፍ መሠረት የሌለው ስለነበር ሀንፈሬ አሊሚራህን የክልሉ ፕሬዝዴንት አድርጎ በመምረጥ ክልሉን ለማረጋጋት ተሞከረ። ክልሉ መረጋጋቱ ሲረጋገጥ ሀንፈሬ አሊሚራህን እንደሰባራ ገል ወረወሩትና እስማኤል አሊ ሲሮን አምጥተው በእሱ ቦታ አስቀመጡ። በዚህ የተከፋው ሀንፈሬ አሊሚራህም የተወሰኑ የALF ታጣቂዎችን በመያዝ በየቡኪ በኩል ወደ ጅቡቲ በመሻገር መሸፈታቸው ተሰማ። ሆኖም ግን፣ ጠላት እንደማይንቅ የሚነገርለት ህወሓት ከሀንፈሬ ጋር በመደራደርና ትጥቃቸውን በማስፈታት የኩዌት አምባሳደር አድርጎ ሾማቸው።

ህወሓት እንዳደራጀው የሚነገረው አዴይም ክልሉን በደንብ መቆጣጠር ቻለ። በርካታ የALF አባላትና ደጋፊዎች የነበሩ ወዳጆቼ ከኃላፊነትና ከሥራ ተፈናቀሉ። የእኔ ደህንነትም ከፍተኛ ስጋት ላይ ወደቀ። አንድ ቀን አመሻሽ ላይ አንድ የፖሊስ ባልደረባ በፀጥታ ኃይሎች ክትትል እየተደረገብኝ እንደሆነ እዚያ ይኖር ለነበረ አጎቴ ሹክ አለው። አጎቴ እንድሪስ መሐመድ (እሱንም አላህ ይራህመው) በእግር በፈረስ ሲፈልገኝ ቆይቶ ሲያገኘኝ “እየተፈለክ ስለሆነ ነገ በሌሊት አይሣኢታን ለቅቀህ መውጣት አለብህ” ብሎ አረዳኝ።

ተይዤ ከመታሰሬ ይበልጥ ያሳሰበኝ፣ የጀመርኩት የቲያትር ዝግጅት መቋረጡ ነበር። አይሣኢታ ከተማ ላይ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በማሰባሰብ ቀደም ሲል በነበረኝ ድርሰት ላይ ተመሥርቼ ቲያትር ማዘጋጀት ጀምሬ ነበር። በዚያ ቲያትር ውስጥ በተዋናይነት ከሚሳተፉት አንዱ ወዳጄ ፈንታው አህመድ ነበር። እኔ አይሣኢታን ለቅቄ የምሄድ ከሆነ የቲያትሩን ጉዳይ ለፈንታው አደራ ሰጥቼ መሄድ ነበረብኝ። ስለሆነም ፈንታው ወደሚገኝበት አፈተ-ከላም ሰፈር ልቤ እየፈራ ጨለማን ተገን አድርጌ በፍጥነት ስራመድ በድንገት “እጅ ወደላይ!” የሚል ድምፅ ከኋላዬ አንባረቀብኝ። ለካስ የፀጥታ ኃይሎች እየተከታተሉኝ ነበር።

ከዚያም በፊት፣ የአድዋ መቶኛ ዓመት በዓል አይሣኢታ ከተማ ላይ ሲከበር በድንገት ተይዤ ለአንድ ሣምንት ያህል ከታሠርኩ በኋላ በአፋር ወዳጆቼ (ወንድሜ Mohammed Oudda Mohammedን ጨምሮ) ጩኸትና ውትወታ ተለቅቄ ነበር። በዚህኛው እሥር ግን በቀላሉ እንደማይለቁኝ ደመ-ነፍሴ ነግሮኛል። እንደፈራሁትም በካቴና አስረው በመውሰድ ቆሞ ከሚጠብቀኝ መኪና ውስጥ አሰገብተው ወደ ደሴ ላኩኝ። በመጀመሪያ ከከተማ አውጥተው ሊገድሉኝ መስሎኝ ሰግቼ ነበር። እኔ እንዳሰብኩት ሰይሆን ለደሴ ከተማ ፖሊስ ወስደው ካስረከቡኝ በኋላ እዚህ የማልዘረዝረው ብዙ እንግልትና ስቃይ ደረሰብኝ። በኋላ በዘመድ-አዝማድ ጥረት ከእስር ተለቅቄ ወደአፋር ተመልሼ ስሄድ “የመዋቅር ማስተካከያ” በሚል የሥራ መደቤ መታጠፉ ተነገረኝ።

ይኸ ነገር ሌላ እልህ ውስጥ እንድገባና ወዳቋረጥቁት ትምህርቴ እንድመለስ በጣም ጠቅሞኛል። ከትምህርቴ በተጓዳኝ የተለያዩ ጋዜጦች ላይ መጻፍ ጀምሬ ነበር። አፋር ክልል ስኖር፣ በተለይ “አይቲሌ ፈራክሱግኔ – ከአፋር) በሚል የብዕር ሥም ጦቢያ መጽሔት ላይ ማቅረብ የጀመርኩትን ጽሁፍ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላም ቀጥዬበት ነበር። በዚህም ሳቢያ፣ አስ-መሐመድ አልጋኔን ጨምሮ ከብዙ የአፋር ወዳጆቼ ጋር እገናኝ ነበር። ከሥመ-ጥሩው የአፋር የፖለቲካና የመንፈስ አባት ከሆኑት ታላቁ ሱልጣን አሊሚራህ (አላህ በጀነት ምቾታቸውን ያብዛላቸውና) የመገናኘት ዕድሉም ነበረኝ። እሳቸውን ብቻ ሰይሆን፣ አሁን ደግሞ ለልጃቸውን ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህንም አጣን።

አላህ ሰብር ይስጣችሁ ወዳጆቼ!!!

LEAVE A REPLY