የሕክምና ተማሪዋን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገደለው ወጣት ወንጀሉን ክዶ ተከራከረ

የሕክምና ተማሪዋን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገደለው ወጣት ወንጀሉን ክዶ ተከራከረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና|| የሕክምና ተማሪ የነበረችው ሃይማኖት በዳዳን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው ደግነት ወርቁ የተጠየቀበትን ወንጀል ክዶ ተከራከረ።

ተከሳሽ ደግነት ወርቁ ግንቦት 17/2012 የ2ኛ ዲግሪ የመመረቂያ ምርምር ሥራዎች በማከናወን ላይ የነበረችው ሃይማኖት በዳዳን በግምት ከቀኑ 8 ሰዐት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል 4ኛ ፎቅ ላይ የነበረችበትን ክፍል ከውስጥ ቆልፎ በስለት ወግቶ ገድሏታል በሚል ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉ አይዘነጋም።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የነፍስ ግድያና ከባድ ውንብድና ችሎት ፤ በከባድ ውንብድና የተከሰሰው ግለሰቡ በእለቱ ከፈጸመው ግድያ ወንጀል ባሻገር፤ የሟችን አይፎን ሞባይል፣ ላፕቶፕ፣ የ5 ሺኅ ብር ቼክ እና ጥሬ ብር ፓስፖርት፣ እንዲሁም የቤት ቁልፍ ዘርፏል በማለት ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶበታል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወንጀሉ እንደተፈፀመ እያወቀ ከተዘረፈው የሟች ንብረት ተጋራ የተባለው ምህረቱ ሚጣ የተባለው ግለሰብም በከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶበታል።
ተከሳሾቹ ወንጀሉን አልፈጸምንም በማለት ክደው መከራከራቸውን ተከትሎ፤ ችሎቱ የዐቃቤ ህግን ምስክር ለመስማት ለህዳር 23/2013 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ኢትዮጵያ ነገ ከታማኝ ምንጮቹ መረዳት ችሏል።

LEAVE A REPLY