ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአፋር መንፈሳዊ መሪ የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ አስክሬን ዛሬ ሰመራ ከተማ ሲገባ አቀባበል ተደረገለት።
የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ፣ የሃይማኖች አባቶች ፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ የቀብር ሥነ ሥርዓት በትውልድ ስፍራቸው አይሳኢታ ዛሬ ተፈጽሟል። ሱልጣኑ ባደረባቸው ህመም የሕክምና እርዳታ ሲደርግላቸው ቆይቶ፣ በተወለዱ በ74 ዓመታቸው ከትናንት በስቲያ ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸው ይታወቃል።
ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ በሃገሪቱ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ በስደት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር። በውጭ ቆይታቸው ለአፋር ሕዝብ በጥቅል ለኢትዮጵያዊያን መብት ሲታገሉና ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ ለውጡን ለማስቀጠል ከህዝባቸው ጋር የተለያዮ ሥራዎችን እየሠሩ ነበር።
ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ህዝባቸውን በመንፈሳዊ መሪነታቸው ያገለገሉ ከማገልገላቸው በተጨማሪ በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነውም ሠርተዋል።