ጃዋር መሐመድ በሽብርተኝነት መከሰሴ ኩራት ቢሆንም፣ ከምርጫ ውድድር ውጭ እንድሆን የታሰበ ነው...

ጃዋር መሐመድ በሽብርተኝነት መከሰሴ ኩራት ቢሆንም፣ ከምርጫ ውድድር ውጭ እንድሆን የታሰበ ነው አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና|| ለሁለተኛ ጊዜ በሽብርተኝነት የተከሰስኩት በቀጣዮ ምርጫ እንዳልሳተፍ ለማድረግ ታስቦ ነው ሲል ጃዋር መሐመድ ተቃውሞውን ገለጸ።

ከድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባና በተለያዮ የኦሮሚያ ከተሞች አመጽና ሽብር ቀስቅሰዋል በሚል ከተጠረጠሩት ግለሰቦች መሀል ዋነኛው ፊታውራሪ ነው የሚባለው ጃዋር መሐመድ  “ለሁለተኛ ጊዜ በሽብር በመከሰሴ ኩራት ይሰማኛል” ሲልም ዛሬ በነበረው የፍርድ ቤት ውሎው ተናግሯል።
ኹከት ናፋቂው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ከዚህ በፊት (በውጭ ሀገር እያለ) በሽብርተኝነት ተከሶ የነበረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ክሳቸው ከተነሳላቸው ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ቢገባም ፤ እግሩ በረገጠበትና የጽንፈኝነት መልእክቱን ባስተጋባበት ቦታ ሁሉ ሰዎች ተዘቅዝቀው ከመሰቀል በቁም እስከመቃጠል ድረስ አስነዋሪና አረመኔያዊ ድርጊቶችን መመልከት የተለመደ ሆኗል ።
ክሱ የተመሰረተብኝ አገራዊ ምርጫው እንዳልሳተፍ ነው ያለው ጃዋር መሐመድ፤ ገዢው ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል እሸነፋለሁ ብሎ በመስጋቱ የሽብር ክስ እንዲመሰረትብኝ ተደርጓል ሲልም ተቃውሞውን ገልጿል።
“እስክንድር ነጋም በአዲስ አበባ ምርጫውን ያሸንፋል ተብሎ ተፈርቶ እንጂ፤ ወንጀል ሰርቶ አይመስለኝም የታሠረው”  ያለው ጃዋር ሌሎች ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ ምን እንደሆነም ችሎቱን ከመጠየቁ ባሻገር፤ አቶ ልደቱ አያሌው ለእስር የተዳረገው የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለው ሃሳባቸው ተሰሚነት እያገኘ ስለነበረ ነው በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል።
ክሱ የተመሰረተባቸው እነዚህ ሰዎች ተጠርጣሪዎች ዛሬ ዝርዝሩ በጽሑፍ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ችሎቱ ክሱን ለመስማት ለፊታችን ሐሙስ መስከረም 14/2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጠ ታውቋል።

LEAVE A REPLY